የወጪ ምርቶቻችን ንግድ ውስጥ የሚፈጸሙ ውሎችን ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው የውል ምዝገባና አፈጻፀም ስርዓትን በመዘርጋት አገራችንን የውል አተገባበር መልካም ገጽታን በመገንባት ምርቶቻችን በውጭ ገበያ ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በወጪ ምርቶቻችን ሽያጭ ላይ የሚፈጸሙ የወጪ ንግድ ውሎችን ባለመፈፀም በተዋዋይ ወገኖች እና በሀገር መልካም የውል አተገባበር ገጽታ ጉዳት በሚያደርሱ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ሀገራዊ መልካም ገጽታን መገንባት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
አላግባብ ለረጅም ጊዜ በክምችት የሚያዙ የወጪ ምርቶች በወቅቱ ተልከው ለአገሪቱ ሊገኝ የሚችለውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በወቅቱ ማስገኘት በማስፈለጉ፤
የወጪ ምርቶች ግብይትን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት የተዋዋይ ወገኖችን እና ሀገራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ በማስፈለጉ፤
የኢ.ፌ.ድ.ሪ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባርን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 19(1-መ) መሠረት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡