ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ ላለፉት አራት ተከታታይ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመታት አገራችን ወደ ውጪ ከላከችው ጠቅላላ የኤክስፖርት መጠን ውስጥ የግብርና ምርቶች በየዓመቱ በቅደም ተከተል 2.75፣ 32፣ 308 እና 3.25 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል፡፡ በመሆኑም የግብርና ምርቶች ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ ድርሻ እያበረከቱ ስለሆነ አስተዋፅኦዋቸውን ይበልጥ ለማሳደግ መንግሥት እያንዳንዱ ምርት በጥራት ቁጥጥርና ግብይት ሥርዓት እንዲመራ ስትራቴጂ በመቀየሱ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት መዳረሻ ገበያ ድረስ ያሉ የግብይት ተዋንያን ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ህገወጥ ንግድን በመከላከልና ህጋዊ ነጋዴውን በማበረታታት አገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማስጠበቅ : ሲባል የአየር መንገድ ተጓዦች ከኢትዮጵያ ሲወጡ ይዘውት መሄድ የሚችሉትን የተለያዩ የግብርና ምርቶችና የፋብሪካ ውጤቶች መጠን ለመወሰንና የሚገጥማቸውን እንግልት ለመቀነስ ይህ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡