ጥራቱን የጠበቀና ተደራሽ የሆነ የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት እንዲስፋፋ ማድረግ ሕዝብን በማስተማር፣ በማሳወቅ እና በማዝናናት ለፈጣንና ቀጣይነት ላለው ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ የሆነውን በመረጃ የበለፀገ ሕብረተሰብ በመፍጠር በአገራችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን በማመን፤
የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ ሒደትን ግልፅ እና ፍትሐዊ እንዲሁም የሃሳብና የመረጃ ብዝሃነትን የሚያስፋፋ እንዲሆን ማድረግ በማስፈለጉ፤
በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 6(1)፣ (5) እና 31(1)(ሀ)፤ መሠረት የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ በመስጠት መገናኛ ብዙሃንን ማስፋፋት እና ባለፈቃዶችም የሙያዊ ሥነ-ምግባር፣ ሕገ መንግስቱን፣ የአገሪቱን ሕጎች እንዲሁም፤ የሕዝብን ሰላም፣ ደኅንነት፣ የዜጎችን ተነፃፃሪ መብቶችና ጥቅሞች ባከበረ መልኩ በኃላፊነት ስሜት ሥራቸውን ማከናወናቸውን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤
በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 12(7) እና አንቀጽ 90(2) መሠረት ይህ መመሪያ በባለሥልጣኑ ቦርድ ወጥቷል፡፡