በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብለክ ህገ መንግሥት አንቀጽ 42(2) ላይ ‹‹ሰራተኞች ጤናማና አደጋ የማያደርስ የስራ አካባቢ የማግኘት መብት አላቸው›› በሚል የተደነገገውን፣ እንዲሁም የስራ አካባቢ ደኅንነትና ጤንነት አጠባበቅ በፌዴራል የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ በፌዴራል የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ውስጥ የተደነገገውን ተግባራዊ ማድረግ በማስፈለጉ፤
የስራ አካባቢ ደኅንነትና ጤንነት አጠባበቅ በማሻሻል የሰራተኞችን ደኅንነትና ጤንነት በመጠበቅ የስራ ብቃት ማጎልበት፣ የስራ ቦታን ለሰራተኞች ደኅንነትና ጤንነት በሚስማማ መልኩ ማዘጋጀት፣ ማደራጀት፣ ማሻሻልና መጠበቅ እንዲሁም መስሪያ ቤቱ /ተቋሙ/ በጎ በሆነ ማኅበራዊ ህይወት ላይተመስርቶ አመርቂ የስራ ውጤት እንዲያስመዘግብ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፤
የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎች የሚባሉት ቁሳቁሶች እንደ እጅ ጓንት፣ ማስክ፣ ሴፍቲ ጫማ እና የመሳሰሉት ሲሆኑ በትክክለኛና በአግባቡ መጠቀም ሰራተኞችን ከተለያዩ አደጋዎች ማለትም ከአካላዊ፣ ስነልቦናዊና አዕምሯዊ፣ ከረቂቅ ተህዋሲያንና ከመሳሰሉት መከላከል የሚያስችል የሚያስችል በመሆኑ፤
አንድ ሠራተኛ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት እንደሥራው ባህሪ ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል ጤንነቱን እና ደህንነቱን ከተለያዩ የሥራ ቦታ አደጋ፣ የጤና ጠንቆችና ጉዳቶች ለመከላከል የሚረዱ የአደጋ መከላከያና እንዲሁም አደጋ ቢከሰት የሚደርሰውን አስከፊ የጉዳት መጠን ሊቀንሱ የሚችሉ መከላከያ መሳሪያዎችን የሥራ መሳሪያዎች ወይም ልብሶች መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ፤
በፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ መሠረት እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶችን ለሠራተኞች የማቅረብና ስለአጠቃቀማቸው መመሪያ የመስጠት ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ፤ ሥራ በመሥራት በሚገኝ ሠራተኛ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መከላከሉ ወይም የጉዳቱን መጠን መቀነሱ የሚወሰነው ሥራው የሚጠይቀውን የመከላከያ መሳሪያዎች አይነት በመለየትና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል በመሆኑ፤ በኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎችን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው፣ የግንዛቤ እጥረት እና ምቹ የሆነ የስራ አካባቢ ባለመኖሩ ለቀላል፣ መካከለኛና እስከ ህይወት መጥፋት ለሚዳርግ አደጋ ተጋልጠው እንደሚገኙ ግንዛቤ የተወሰደ በመሆኑ፤
በሠራተኞች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ወይም የሚደርሱ የአደጋና የጤና ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል እንዲያስችል ከሲቪል ሰርቪስ ኪሚሽን የአደጋ መከላከያ መሣሪያዎች፣ ደንብ ልብስ እና ፕሮቶኮል አሰጣጥ በተመለከተ በ2000 እና በ2011 ዓመት የወጡ መመሪያዎችን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን አዋጅ እና የተለያዩ የሥራ አካባቢ ጤንነትና ደኅንነት በተመለከተ የተዘጋጁ ጽሁፎችን በማገናዘብ የፌዴራል የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት በኢንስቲትዩቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1071/2010 አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ (2) መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡