በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ ቁጥጥር እና የቅጣት አፈፃፀም ሂደት ወጥነት ባለው መልኩ እንዲከናወን የአሠራር ስርዓት መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ በዘርፉ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
በተሻሻለው የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎች በሚፈፅሙት ጥፋት ምክንያት የሚጠብቃቸው ቅጣት ከገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ የጥፋት ነጥብ እንዲመዘገብ በማድረግ አሽከርካሪዎችን ለተወሰኑ ጊዜያት ከማሽከርከር ለማገድ የሚያስችል ስርዓት የዘረጋ በመሆኑ እገዳው የሚመራበት የአሠራር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ደንብ ቁጥር 27/2002 አንቀጽ 5 መሠረት የትራፊክ ተቆጣጣሪ መስሪያቤት የትራፊክ ደንብን በማስፈፀም ሂደት ውስጥ ሊከተል የሚገባውን ስርዓት ያስቀመጠ ቢሆንም ዝርዝር አፈፃፀሙን በመመሪያ መወሰን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀትና ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 64/2011 አንቀጽ 49(11) መሠረት የትራፊክ ደንቦች መከበራቸውን ቁጥጥር እንዲያደርግ፣ አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ደንብ ተላላፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ፣ የማስፈፀሚያ ስልቶችን እንዲዘረጋ እና ተግባራዊነታቸውን እንዲያረጋግጥ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በከተማችን ውስጥ የሚከናወኑ የትራፊክ ቁጥጥር ስራዎች ስርዓት ባለው መልኩ እንዲፈፀሙ የትራፊክ ቅጣት አፈፃፀም አሠራርን በሕግ መወሰን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ አስተዳደሩን አስፈፃሚ አካላት እንደገና ለማደራጀት እና ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው በአዋጅ ቁጥር 64/2011 አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 3 (ሠ) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህን የትራፊክ ቅጣት አፈፃፀም የአሠራር መመሪያ አውጥቷል፡፡