በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል የሚፈጠሩ የፍትሐብሄር አለመግባባቶች የሕዝብና የመንግሥትን ሀብት በሚቆጥብ፣ ቀልጣፋ በሆነ፣ የተቋማቱን መልካም ግንኙነት በሚጠብቅ እና ተቋማቱ በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነቶች በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ በሚያግዝ መንገድ መፈታት ያለባቸው በመሆኑ፤
ፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች እርስ በርሳቸው ባልተግባቡበት የፍትሐብሄር ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40(2) (ሀ) መሠረት ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ፤
የፍትሕ ሚኒስቴር አለመግባባቶችን ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ተግባራዊ ማድረግ የሚገባውን ግልፅ እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ የአሠራር ሥርዓት፣ የክርክር መፍቻ አማራጭ መንገዶች እና የክርክር አመራር ሥርዓት ደንብ በመመሪያ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የፍትሕ ሚኒስቴር በአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 19(4) ስር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል።