ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው ለሳይንስና ለምርምር፣ ለኤኮኖሚያዊ ልማትና ለባህል እድገት የጎላ አስተዋፅኦና ጠቀሜታ ሊያበረክቱ በሚችሉበት መንገድ በባህል ተቋማትና ማዕከላት በማሰባሰብ ማደራጀት ተገቢ በመሆኑ፣
ምትክ የሌላቸውንና የሕዝቦቻቸንን ማንነት ዓይነተኛ መገለጫዎች የሆኑ የታሪክና የባህል ቅርሶችን በማሰባሰብ ከማንኛውም ዓይነት ጉዳትና ጥፋት በማዳን ለትውልድ ማቆየት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ሀገራዊ ጉዳይ ስለሆነ፣
የአንድን የቅርስ ስብስብ ማእከል የቅርስ ክምችት በተገቢው ዓይነትና መጠን በማሳደግ ሀገራዊ ደረጃውን እንዲጠብቅ ለማድረግ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው የተጠናከረ የቅርስ ማሰባሰቢያ ሥርዓት መዘርጋትና የአፈፃፀም ስልት በመቅረፅ ሥራ ላይ ማዋል በመሆኑ፣
የቅርስ ከምችቶች ስፋት ባለው ብሔራዊ ተዋፅኦ ላይ ተመስርቶ ቅርሶችን ማሰባሰብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ በአዋጅ ቁጥር 209/1992 አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ይህ መመሪያ ወጥቷል፡፡