የከተማ, ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሰራዊት ገንብቶ በልማት ሠራዊት ኃይል የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ራዕይና ተልዕኮ ለመሣካት እና የዘርፉን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በየምዕራፉ በላቀ ደረጃ ለማስፈጸም ሚኒስቴር መ/ቤታችን ጠንካራ የመንግሥት ክንፍ በመፍጠር አመራሮችና ፈጻሚዎች ቆጥረው በማቀድ፣ ወደ ተግባር በመግባት ቆጥረው በመፈጸም የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እያንዳንዱ አመራርና ፈጻሚ በምን ደረጃ ዕቅዱን አሳክቶ ኃላፊነቱንና ተልዕኮውን እንደተወጣ መለካትና በውጤታቸው መሠረት ደረጃቸውን በመለየት ጥሩ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ግንባር ቀደም አመራሮችና ፈጻሚዎች የሚበረታቱበት እና ደካማ አፈጻጸም ያስመዘገቡትን ለማሻሻል የሚያስችል ተገቢ ድጋፍ የሚሰጥበት አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ በአፈጻጸም ሂደት የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታት ማነቆዎች በምዘና ሂደት በግልጽ ተለይተው በየደረጃው ባለው የሰራዊት ግንባታ አደረጃጀት በዕቅድ ተይዞ ሊሰራባቸው ይገባል፡፡
በዚሁ መሠረት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የአፈጻጸም ምዘና ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 9/2004 ሐምሌ 2004 ማዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአፈጻጸም ሃደት መመሪያው የማይዳስሳቸው ጉዳዮች በማጋጠሙ ምክንያት የአመራርና ፈጻሚ ምዘናን ሙሉ ከማድረግ አንጻር እነዚህን ጉዳዮች ማካተት አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ይህ የተሻሻለው መመሪያ የቀድሞ መመሪያ ክፍተቶችን ከመድፈኑም ባሻገር ግልጽና ወጥነት ያለው አሠራር በመፍጠር በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቅልጥፍናን በማበረታታ በግልጽነት፣ በተጠያቂነት እና በውጤታማነት መርህ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት እና እርካታን ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመሆኑም የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና መመሪያን እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የተቀናጀ የውጤት ተኮር ስርዓት በማጣጣም ይህ የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የአመራርና ፈጻሚ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ማስፈጸሚያ መመሪያ ተሻሽሎ ተዘጋጅቷል፡፡