የባህል ኢንደስትሪ ዘርፍ በሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ ላይ ምርታማና የልማት ተዋንያን ዜጎችን በማፍራት፤ ዘርፉ በሰብዓዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ያለውን ሚና ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ፤
የዘርፍ ሙያተኞች ሙያቸውንና ክህሎቶቻቸውን በመጠቀም ባህላዊ እሴቶች እንዲታወቁ፣ እንዲሰራጩና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ የኅብረተሰቡን መንፈሳዊ ሕይወት በማደስና በማነጽ ለሀገሩ ተቆርቋሪ፤ ለወገኖቹ አለንታ በልማት ተግባሩም በንቃት ተሳታፊ የሚሆን ስብዕና በመቅረጽ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፤
የዘርፉን የልማት ተዋናዮች ማበረታታት የሀገራችንን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ብዝሃ ባህል ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ለማስተዋወቅ የሚያስችል አቅም የሚፈጥር በመሆኑ፤
በዘርፉ የላቀ ውጤት ለሚያስመዘግብ የፈጠራ ሰዎች አቅም በፈቀደ መጠን ቁሳዊና ሞራላዊ ማበረታቻ እንደሚደረግ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 91(3) የተደነገገና እና በባህል ፖሊሲው ክፍል 7(1) ቃል የተገባ በመሆኑ፤
በዘርፉ ሽልማት መስጠት የባህል ኢንደስትሪዎች ጠቀሜታ እንዲጠናከር እና የፈጠራ ሥራዎች አድገው እንዲበራከቱ መንገድ የሚከፍት በመሆኑ፤ ሀገር አቀፍ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት በማካሄድ በኢንዱስትሪው የሚገኙ ባለሙያዎችን በማበረታታት በየሥራዎቻቸው አርዓያነታቸውን ለይቶ ዕውቅና መስጠት፤ ለበለጠ ፈጠራና ለመልካም ውጤት በማነሳሳት በጥረት ላይ የተመሠረተ የውድድር ስሜት እንዲኖር ማድረግ ተገቢ በመሆኑ፤
ለሀገር አቀፍ የሽልማት አሰጣጥ የተጠና፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት መከናወን ያለበት በመሆኑ፤
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 31 የተሰጡትን ተግባርና ኃላፊነቶች በአግባብ ለመወጣት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡