የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት ሠጪዎች ሕዝብን ለማሳወቅ፣ ለማስተማርና ለማዝናናት እንዲሁም የዜጎችን ሃሳብና አመለካከት ለማስተናገድ በሚያሠራጩት ፕሮግራም የሌሎችን ሰዎች መልካም ስም፣ ክብር፣ መብትና ጥቅም የሚነኩ ይዘቶችን ሊያሰራጩ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል በማመን፤ መገናኛ ብዙኃኑ በኃላፊነት ስሜት የዜጎችን መብትና ጥቅም አክብረው ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ አንፃር የሕዝቡን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በመገናኛ ብዙሃን በተላለፈ ፕሮግራም መልካም ስሜ፣ ክብሬ፣ መብቴና ጥቅሜ ተነክቷል ወይም ይዘቱ ሕግን የሚጥስ ነው፤ እንዲሁም ከአገር፣ ከሕዝብ ጥቅም ወይም ከሌሎች መሰል መለኪያዎች አንፃር ሲታይ ይዘቱ ጉድለት አለበት የሚል ግለሰብና ተቋም ሲኖር፤ ቅሬታውን ለመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት ሠጪው እና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን በማቅረብ ውሳኔ የሚያገኝበትን ሕጋዊ አሠራር መዘርጋት በማስፈለጉ፤
በባለሥልጣኑ የሚካሄደው ቅሬታ አቀባበል፣ ምርመራና ውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ራሳቸውን በቻሉ የቅሬታ እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች እንዲከናወን በማድረግ የቅሬታ አቅራቢዎችንም ሆነ የመገናኛ ብዙሃንን መብት የሚያረጋግጥ፣ ተጠያቂነት የሠፈነበት፤ ግልፅና ታማኝ አሠራር እንዲሰፍን ማድረግ በማስፈለጉ፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የሚተዳደሩበትን የሙያ ሥነ-ምግባር ደንብ የሚያወጡበትን፣ የዘርፉን የሙያ ብቃት የሚያሳድጉበትና የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ቅሬታዎች የሚያስተናግዱበትን አሠራር በመዘርጋት በተቋም ደረጃም ሆነ በጋራ ራሳቸውን ለሕዝቡ ተጠያቂ አድርገው እርስ በእርስ የሚተራረሙበትን ሒደት ማጠናከር በማስፈለጉ፤ እንዲሁም
በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 6(5)፣ (6)፣ (7)፣ 12(5)፣ (6)፣ 50 እና 67 መሠረት የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎትን በተመለከተ በግለሰቦችና በተቋማት የሚቀርቡ ቅሬታዎችን እንዲሁም በባለፈቃዶች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን መርምሮ ፈጣንና ሕጋዊ ውሳኔ መስጠት በማስፈለጉ፤ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 12(7) እና አንቀጽ 90(2) መሠረት ይህ መመሪያ በባለሥልጣኑ ቦርድ ወጥቷል።