ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከተጣለበት ኃላፊነት አንፃር ዓለምአቀፍ ሕግጋትና ድንጋጌዎችን እንዲሁም ተቀባይነት ያላቸውን ደንቦችን መሠረት በማድረግ ተልዕኮውን ለማሳካት የሚያስችል ሙያዊ ብቃትና አቅም ያለው ሠራተኛ በማሰማራት ውጤታማ አገልግሎትን ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ ባለስልጣኑ የሚሰጠው አገልግሎት ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ተፈላጊውን እውቀትና ክህሎት ያዳበረ ባለሙያ ለማቆየትም ሆነ ለማበረታታት ግልፅና ፍትሐዊነትን የተላበሰ የደረጃ እድገት አሰጣጥ ሥርዓትን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡
በባለሥልጣን መ/ቤቱ ከሐምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰራበት የሚገኘው የደረጃ እድገት አሠራር መመሪያ በአዲስ መልክ ከወጣው አዋጅ ቁጥር 1064/2010 እና ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር ፐ/ሰ/ሚ30/ጠ5/14/228 የተላለፈው የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የምልመላና መረጣ አፈፃፀም መመሪያ አንፃር በመሠረታዊነት መካተት ያለባቸውን ነጥቦት በማካተት ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበትን የደረጃ እድገት አሰጣጥን አጠናክሮ ለማስኬድ እንዲቻል በአዲስ መልክ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም በግልፅ ሊመዘን የሚችል የውጤት አለካክ ሥርዓትን መሠረት በማድረግ እንደየሥራ መደቡ ባህርያት በይበልጥ ነጥብ ሊሰጠው የሚገባውን የማወዳደሪያ መስፈርት በመለየት የያዘ የአሠራር መመሪያ በመጠቀም ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሳደጉ የሥራ ተነሳሽነታውን የሚያጐለብት ከመሆኑም በላይ ሠራተኞችን/ባለሙያዎችን ለማቆየትና ተተኪዎችን ለመፍጠር ያስችላል፡፡
በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የምልመላና መረጣ አፈፃፀም መመሪያን መሠረት በማድረግ የሙያ መሰላልን ጠብቆ ከሚሰጠው የደረጃ እድገት ውጪ ለሚገኙ የድጋፍ ሰጪ፣ የኤርናቪጌሽን አገልግሎትና የአቪዬሽን ሬጉሌሽን የሥራ መደቦች የደረጃ እድገት የማወዳደሪያ መስፈርት ተዘጋጅቷል፡፡