በሆስፒታሎች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃውን የጠበቀና በሥርዓት የሚመራ እንዲሆን ለማስቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጤና አገልግሎት አሰጣጥ አስተዳደርና አመራር የተሻሻለዉ አዋጅ 08/2001 በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ማጽደቁ ይታወቃል።
ይህንኑ አዋጅ ይበልጥ ለማብራራትና ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲረዳ በማሰብ የከተማ አስተዳደሩ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ አስተዳደርና አመራር ደንብ 26/2001 በካቢኔ ወጥቷል። መመሪያ ቁጥር 1/2001 እንዲሁም ልዩ ልዩ የ አፈጻጸም ማኑዋሎች በከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ማውጣቱ ይታወሳል በዚህም የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በመንግሥት ሆስፒታሎች የግል ህክምና ክፍል አገልግሎት አሠራርና አደረጃጀት ሰፍሮ ይገኛል፡፡
የዚህ አገልግሎት መጀመር የባለሙያዎችን የስራ ተነሳሽነት በመጨመርና ባለበት ሆስፒታል ረጅም ጊዜ ቆይተው እንዲያገለግሉ ከማስቻሉም በላይ ለህብረተሰቡ አማራጭ የህክምና አገልግሎት ሆኗል።
ይሁን እንጂ በአሠራሩ ላይ በተደረጉ ጥናቶች የአላቂ እቃዎች ሆስፒታል የሚመለሱበት ሥርዓት አለመኖር፣ የግል ህክምና አገልግሎት በመደበኛ የህክምና አገልግሎት ሰዓት መሥራት፣ የሰው ሃይል አመዳደብ መርህ አለመኖር፣ የአገልግሎት ዋጋ ወጥ ያለመሆን ፣ የገቢ ትርፍ ክፍፍል ሥርዓት አለመኖር እና የመሳሰለት ችግሮች የተስተዋለ በመሆኑና ከተጠቃሚው ህብረተሰብ በሚነሱ ጥያቄዎች መሠረት ከዚህ በፊት በወጣው መመሪያ ላይ ያልተሸፈኑ ሁኔታዎችን ለማብራራትና የዋጋ ትመና ጣሪያ ለማስቀመጥ መመሪያውን ማሻሻል በማስፈለጉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ይህ የማሻሻያ መመሪያ ወጥቷል።