የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር አብሮ በመጓዝ ከምድር ወደ አየር፣ ከኬብል እና ከሳተላይት የማሰራጫ መንገዶች በተጨማሪ በበይነ-መረብ አማካኝነት በስፋት በመሰራጨት አማራጭ የመረጃ ምንጭ፣ የአመለካከትና የሃሳብ ብዝኃነት ማስተናገጃ፣ የልዩ ልዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ማከናወኛ እንዲሁም የገቢ ማስገኛ ዘዴ መሆኑን በመገንዘብ፤ ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር የሚጣጣም መመሪያ በማውጣት የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኃንን ዕድገት ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤
ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን፣ ሃሳቦችንና አመለካከቶችን በነፃ ማንሸራሸራቸውን ከማረጋገጥ፣ ጥበቃ ከማድረግ እንዲሁም የዘርፉን እድገት ከማረጋገጥ አንፃር በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 የተዘረጋውን የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን የምዝገባ፣ የክትትልና ድጋፍ አሰራሮች በዝርዝር መመሪያ ማስፈፀም በማስፈለጉ፤
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 6(3) እና አንቀጽ 27 መሠረት በበይነ-መረብ አማካኝነት የሚሰራጩ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ወይም የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን ይዘት አሰራጮች ማንነታቸውን በይፋ እንዲገልጹ ወይም በባለሥልጣኑ እንዲመዘገቡ በመደንገጉ፤ የምዝገባ ሥርዓት ሒደቱን ግልፅ፣ ፍትሐዊ፣ የሃሳብና የመረጃ ብዝኃነትን የሚያስፋፋ ማድረግ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ አንቀጽ 6(5) መሠረት የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሠጪዎች የአገሪቱን ሕጎች ባከበረ መልኩ ሥራቸውን ማከናወናቸውን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤
በተመሳሳይም የባለሥልጣኑን የሥልጣን ክልል በግልፅ በመመሪያ መወሰን በማስፈለጉ፤
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 12(7) እንዲሁም አንቀጽ 90(2) መሠረት ይህ መመሪያ በባለሥልጣኑ ቦርድ ወጥቷል፡፡