መንግሥት በከተሞች የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገትን ለማፋጠን ከቀየሳቸው ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ በመሆኑና ስትራቴጂውን በብቃት ለመፈጸም ብቁ የሰው ኃይል፣ ተፈላጊና አዋጭ ቴክኖሎጂ አቅርቦትና የአሠራር ስርዓት ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ፣
በሀገሪቱ የሚገኙ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ገበያን መሠረት ያደረጉ እና በጥራት፣ በምርታማነት፣ በጊዜና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንዲችሉ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ እና በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂው በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ለመስጠት የሚያስችል የአሠራር መመሪያ በ2003 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ባለፉት አመታት ተግባራዊ በመደረጉ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡ መሆናቸውን መገንዘብ የተቻለ በመሆኑ፣
በየደረጃው ያሉ አስፈፃሚ አካላት ማለትም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ፣ የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲና የአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ተቀናጅተው ያላቸውን የሰው ኃይል አቅም በማጐልበትና ሀብታቸውን በማንቀሳቀስ በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ብቁና ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዞች ለማፍራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ከአዲሱ የኤጀንሲው ተልዕኮ እና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ከዚህ ቀደም ይሰራበት የነበረውን የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ የነበሩትን ክፍተቶች ለመሙላት በሚያስችል መልኩ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ መሠረት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ መመሪያ የኢንተርፕራይዞችን የዕድገት ደረጃ እና የኤጀንሲውን ተልዕኮ ታሳቢ ያደረገና ወጥነት ያለው ሞዴል መመሪያ ማዘጋጀት በማስፈለጉ እንዲሁም በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ለሁሉም ኢንተርፕራይዞች የሚያስፈልገውን ድጋፍ ከኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ፣ አሳታፊ፣ ፍትሃዊና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ይቻል ዘንድ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 374/2008 አንቀጽ 14 መሠረት ይህ ሞዴል መመሪያ ተሻሽሎ ተዘጋጅቷል።