ኢትዮጵያ ለባለፉት ዘጠኝ ዓመታት እያስመዘገበች ባለዉ ፈጣን ዕድገት ሳቢያ በተፈጠረው የኢኮኖሚ መነቃቃት ወደ አገር ውስጥ የምታስገባቸውም ሆነ የምትልካቸው ዕቃዎች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡ ይኸም ዕድገት በአጭር ጊዜ ውስጥ በእጥፍ እንደሚያድግ ይገመታል፡፡ በአንፃሩ ዕቃን ከወደብ የማንሳት አቅማችን በዚያው መጠን ባለማደጉ እና ከአስመጪው ጀምሮ በሂደቱ ተዋናይ በሆኑ አካላት ላይ ከሚታዩnድክመቶችና ችግሮች፡ የማጓጓዝ ሥርዓቱ ፈጣን ካለመሆኑ የተነሳ በአገር ዉስጥ በቂ የማከማቻ መጋዘን ባለመኖሩ የገቢ ንግድ ዕቃዎቻችን ለከፍተኛ የመጋዘን ኪራይ እና ከቆይታ ብዛት ለብልሽት ከመጋለጣቸዉም በላይ ለወደብ መጨናነቅ ዕቃዎች በተገቢ ጊዜ አገር ዉስጥ ገብተው ለተገልጋዩ አለመድረስ ከዚህም ጋር ተያይዞ ለሚፈጠር የዕቃዎች እጥረት የዋጋ ዉድነት፣ፋብሪካ ምርቶች መቋረጥ የግንባታዎች መዘግየት እንዲሁም ለልዩ ልዩ አላስፈላጊ ወጪዎችና መሠል ጉዳቶች እንዲከሰቱ ምክንያት በመሆን ላይ ነው፡፡ከዚህም ባለፈ ዕቃዎች ወደብ ላይ ከ6 ወር በላይ በመቆየታቸው በወደብ ተወርሰው በጨረታ የመሸጥ ሁኔታ የሚደጋገም ክስተት የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
ስለሆነም እነዚህን ችግሮች እና ማነቆዎች ለመፍታት ተገቢ የሆነ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ለተግባራዊነቱ መጣር ግድ ከማለቱም በላይ የአገራችን የገቢ ዕቃዎች በወደብ ላይ ለረጅም ጊዜ የማይከማቹበትን አሠራር በመዘርጋት ከገቢ ዕቃዎች ጋር ተያይዘዉ የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት አስፈላጊ ነዉ፡፡
የአገራችንን የገቢ ዕቃዎች ንግድ ልማት ለመደገፍ መከናወን ካለባቸው ቁልፍ ተግባራት ውስጥ አንዱ የትራንዚት ወጪና ጊዜን ለመቀነስ የሚያስችል የትራንዚት
ሥርዓት እና የገቢ ዕቃዎችን ወደ አገር ዉስጥ በአጭር ጊዜ ለማጓጓዝ የሚያስችልየአሠራር ሥርዓት መመሪያ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የአገሪቱ የገቢ ንግድ በተፈላጊ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ የተረጋገጠ፡ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀልጣፋ የወደብና የትራንዚት አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል እንዲሁም የገቢ ዕቃዎችክምችት እንዳይኖር የሚያደርግ የአሠራር መመሪያ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ የገቢ ንግዳችንን ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ያለዉ ማድረግ የግድ ይላል፡፡
በዚህ መሠረት የገቢ ዕቃዎች ትራንዚትን ሂደት ለመከታተል የሚያስችል አሠራርየሚመራበትን ስታንዳርድ እና አሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እና የሚመለከታቸው አካላት እስካሁን ተግባራዊ እያደረጉ የቆዩት ተግባርና ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የገቢ ዕቃዎች ከወደብ በአፋጣኝ የማንሳት ዓላማ ለማሳከት ይቻል ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነቶችና ግዴታዎች ለመወሰን ይህ መመሪያ ወጥቶ ሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፡፡ይህ መመሪያ በማሪታይም ዘርፍ አስተዳደር አዋጅ ቁ.549/1999 አንቀጽ 6 ሥር በተደነገገው መሠረት በወደብና በትራንዚት ኮሪደር በሚካሄደው የአገሪቱ የወጪ እና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በተለይም የአገሪቷን የገቢ ዕቃዎች እንቅስቃሴ ኢኮኖሚያዊነት፣ቀልጣፋነት ለማረጋገጥ እና ለመቆጣጠር እንዲሁም የትራንዚት
አገልግሎት ሥርዓት እንዲሳለጥ የገቢ ዕቃዎች ወደብ ላይ እንዳይከማቹ በሚቻልበት አግባብ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው እንዲሠሩ የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የመምራት ኃላፊነት በተጣለበት የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን አስፈጻሚነት ነው፡፡
በዚህ መሠረት የገቢ ዕቃዎች የትራንዚት ሥርዓት መመሪያ እና የአሠራር ስታንዳርድ ተግባራዊ ለማድረግ እና የሚመለከታቸው አካላት የገቢ ንግድ ልማት መስኩ የታለመለትን ዓላማ ያሳካ ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነቶችና ግዴታዎች ለመወሰን በማሪታይም ዘርፍ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 549/1999 አንቀጽ 18 (ለ) ለሚኒስቴሩ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህ መመሪያ ወጥቷል፡፡