በፌደራል አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 እና በሌሎች ሕጎች መሠረት የተቋቋሙ የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች በተፈቀደላቸው አዲሱ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት የሠራተኞች ድልድል እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በዚህ የአደረጃጀት መዋቅር ማሻሻያ ምክንያት ምደባ የማያገኙ ሠራተኞች የሚስተናገዱበት ስርዓትን በተመለከተ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በ8ኛ መደበኛ ስብሰባ ተወያይቶ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ/ም በቁጥር 6/መ8/ው46/2014 ያስተላለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ፤
መስሪያ ቤት መስሪያ ቤቶች በየትኛውም ተቋም ትርፍ የሰው ኃይል ሲኖር ወይም መስሪያ ቤት ከተዘጋ ወይም የስራ መደብ በመሰረዙ ምክንያት ወይም በመንግሥት ሲታዘዝ በፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 30 መሠረት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በማንኛውም መንግሥት መስሪያ ቤት ባሉት ክፍት የስራ መደቦች ላይ ሠራተኞችን ለመመደብ እንደሚችል የተደነገገ በመሆኑ እና ይህን ድንጋጌ ለማስፈጸም መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 502/2014 መሠረትም የሰራተኞች ስራ ስምሪትና አስተዳደር ስራን ለማከናወን ኮሚሽኑ ለመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውክልና መስጠት እንደሚችል የተመለከተ በመሆኑ በክፍት የሥራ መደቦች ላይ ዝቅተኛ ተፈላጊ ችሎታ የሚያሟሉና በድልድል ያልታቀፉ ሰራተኞችን የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በራሳቸው እና በተጠሪ ተቋማት አወዳድረው እንዲመድቡ ለማስቻል መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 97 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡