በኢትዮጵያ ፈጣን የከተሞች ዕድገትን ተከትሎ የከተማ ነዋሪዎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እና ትብብር በማጠናከር፣ መልካም ተሞክሮዎችንና ልምዶችን በማስፋፋት፣ እንዲሁም የከተሞችን እሴቶች በማስተዋወቅና በማጎልበት ጠንካራ መሠረት ያለዉ የከተማ ሕዝብ ንቅናቄና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻል ዘንድ በየዓመቱ የከተሞች ሣምንት በሚል ሲከበር የቆየ ሲሆን ከ2007ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም በሚል መከበር የጀመረ ሲሆን ይህ የከተሞች ፎረም በየዓመቱ ሳይሆን በየሁለት ዓመት እንዲከበር በመወሰኑ በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም እንደወቅታዊ ሁኔታው የሚለዋወጡ መሪ ቃሎችን በመጠቀም ይከበራል፡፡
የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ዓላማን ለማሳካት ከሚከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሴሚናርና የፓናል ውይይት ዝግጅት አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዝግጅት በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎች አፈጻጸምና ተግዳሮቶች ላይ እና ከዘርፉ ስራዎች ጋር ተዛማጅ የሆኑ የጥናት ጽሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን በዘርፈ ብዙ ጉዳዮችና በተመረጡ የዘርፉ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ የፓናል ውይይት ይካሄዳል፡፡
እነዚህ የፓናል ውይይቶች የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን የትኩረት መስክ በሆኑት የከተማ ልማት ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ዙሪያ በከተማ ልማት ባለድርሻ አካላት ዘንድ የጋራ መግባባትን እና ትክክለኛ ግንዛቤን ለመፍጠር ከሚኖራቸው ከፍተኛ ፋይዳ አንጻርም በርካታ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ በዚሁ መሠረት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የቢሮ ኃላፊዎች፣ዳይሬክተሮች፣ የክልል እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ቢሮ ኃላፊዎችና ምክትል ኃላፊዎች፣ የሥራ ሂደት ባለቤቶች፣ የከተማ ከንቲባዎችና ስራ አስኪያጆች፣ተጋባዥ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወካዮች፣የክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ኃላፊዎች፣የክልል የሙያብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ኃላፊዎችና በማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ሙያዎች የባለሙያዎች ምዘና ወቅት ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉ የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ የተለያዩ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ፎረሙ ከሚካሄድበት ከተማ አስተዳደር ልዩ ልዩ ክፍሎች የተመረጡ ነዋሪዎች፣ በከተማው አቅራቢያ ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ የተመረጡ ተማሪዎች፣ በከተማ ልማትና ቤቶች ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪል ማህበራት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የተለያዩ እህት ከተሞች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች በዚህ ውይይት ላይ የሚገኙ ይሆናል፡፡
በመሆኑም ይህንኑ የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ላይ የሚካሄደውን የፓናል ውይይት ግልጸኝነትና አሳታፊነት ባለው መልኩ ለማስፈጸም እና ከፓናል ውይይቱ የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት እንዲረዳ ይህ የማስፈፀሚያ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡