የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በአዋጅ ቁጥር 555/2000 ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በአዋጅ 47/67 የተወረሱ ቤቶች፣ የገነባቸውን እና ያስገነባቸውን የመኖሪያ እና የድርጅት ቤቶች በማስተዳደር፣ የማከራየት፣ ውል የማደስ፣ የኪራይ ገቢ መሰብሰብ፣ የቤቶችን ጥገናና ዕድሳት ሥራ መሥራት፣ ከኤጀንሲው እጅ ለሚወጡ ቤቶች የግምት ትመናና ቤቶችን የማስተላለፍ ሥራ በአጠቃላይ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ በመሆኑ ከእነዚህ ሥራዎች ዋንኛው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው የጥገናና ዕድሳት ሥራ በመሆኑ፣
ኤጀንሲው የሚያስተዳድራቸው ቤቶች ከሰጡት አገልግሎት አንፃር ከፍተኛ የሆነ የጥገና ሥራ የሚጠይቁ በመሆኑ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በተደረገው የሱፐርቪዥን ጥናት የጥገና አገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል እንዳለበት ስለታመነበትና የነበረው መመሪያም በአዋጁ መሠረት በከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሳይፀድቅ ስራ ላይ የዋለ በመሆኑ ምክንያት እንዲታገድ በመደረጉ የጥገናና ዕድሳት ማሻሻያና ተጨማሪ ሥራዎች ማስፈፀሚያ መመሪያ በአዋጁ መሠረት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማውጣት በማስፈለጉ፤
የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 555/2000 አንቀጽ 11(2) መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡