የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 398/2009 ሲቋቋም ከተሰጡት ዓላማዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ለተለያየ ዓላማ የሚውሉ ቤቶችን መገንባት፣ የፌዴራል መንግሥት ቤቶችና ይዞታዎችን ማስተዳደር፣ ማከራየት፤ በሕግ አግባብ መመዝገባቸውንና መጠበቃቸውን ማረጋገጥ፤ ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ስርዓትን በመዘርጋት ሥራ ላይ ማዋል እና በመንግሥት ቤቶችና ይዞታዎች ላይ የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶችን መከላከልና አስፈላጊ ህጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የመንግሥትን ጥቅም የማስከበር ዓላማዎች ለመፈጸም የተቋቋመ መሆኑ፣
ኮርፖሬሽኑ በአዲስ መልክ ከመደራጀቱ በፊት በተለያየ አደረጃጀትና ስያሜ የቆየ ሲሆን በዚህ ሂደት በቤቶች አስተዳደር ረገድ በርካታ ችግሮች ሲፈታተኑት ቆይቷል፡፡ በተለይም የቤት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት፣ በኮርፖሬሽኑ ቤቶችና ይዞታዎች ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች፣ በመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ሰፊ ክፍተቶች፣ ከቤቶች አከረያየትና ውል አፈጻጸም ጋር እና ሌሎች ከቤቶች አስተዳደር ሥርዓት ማዘመን ያለመቻል ጋር ተያይዞ የሚንጸባረቁ ችግሮች ጎልተው የሚታዩ በመሆኑ፣
ኮርፖሬሽኑ የቤቶች አስተዳደር ስርአቱን የሚመራበት በቀድሞው አደረጃጀት (የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ) የቤቶች አስተዳር መመሪያ ቁጥር 41/2007 በቀድሞው ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጸደቆ እስካሁን በተግባር ላይ የሚገኝ ቢሆንም መመሪያው የተለያዩ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ የቤት አስተዳደሩን በሚፈለገው መጠን በተደራጀና በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመምራት አላስቻለም፡፡ እንዲሁም ከአደረጃጀቱ ለውጥ ጋር በተያያዘ መመሪያው ወቅታዊ መሆን የሚጠበቅበት በመሆኑና በመመሪያው ላይ የሚታዩ ችግሮችንም መፍታት የሚጠበቅ በመሆኑ፣
ኮርፖሬሽኑ በቤት አስተዳደሩ ረገድ የሚታዩ እነዚህን ችግሮቸን ለመፍታትና የተሰጡትን ዓላማዎች ለማሳካት እንዲሁም የሚመራበት የቤት ኪራይና አስተዳደር ሥርዓት ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ መዘርጋት በማስፈለጉ፣ የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1984 አንቀጽ 14(4) መሠረት ይህንን የቤቶች አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 02/2010 አውጥቷል፡፡