የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በሕግ ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሰላሳ ዘጠኝ ዓመታት በአዋጅ የተወረሱና እራሱ የገነባቸውንና ያስገነባቸውን የመኖሪያና የድርጅት ቤቶችን ሲያስተዳድር ከቆየ በኋላ፣ በአዋጅ ቁጥር 555/2000 በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የሚያከራያቸውን ቤቶችን የተለያዩ አስተዳደራዊ ስራዎች ማለትም የማከራየት፣ ውል የማደስ፣ የኪራይ ገቢ መሰብሰብ፣ ለቤቶች የጥገናና እድሳት ስራ የመሥራት፣ ለአፓርትመንት ቤቶች የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት፣ በተለያየ ምክንያት ከኤጀንሲው እጅ ለሚወጡ ቤቶች የግምት ትመናና ቤቶችን የማስተላለፍ ስራዎችን የሚያከናውን በመሆኑ፣
ኤጀንሲው እነዚህን አስተዳደራዊ ስራዎችን በሚያከናውንበት ሃደት ውስጥ በርካታ ክፍተቶች እንደነበሩበት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባካሄደው የሱፐርቪዥን ጥናት በመረጋገጡ ምክንያት፤ በተለይ ኤጀንሲው አውጥቶአቸው ይስራባቸው የነበሩት ልዩ ልዩ መመሪያዎች በአዋጁ መሠረት ህጋዊ አሠራር ተከትለው ሳይፀድቁ ስራ ላይ የዋሉ፣ ግልፅነት የጎደላቸውና ለተለያዩ ብልሹ አሰራሮች የተጋለጡ ስለነበሩ እንዲታገዱ በመደረጉና ይህንንም ችግር በሚፈታ መልክ አዲስ መመሪያ በአዋጁ መሠረት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማውጣት በማስፈለጉ፣
የኤጀንሲውን ቀጣይ ተልእኮ የሚወስን የቤቶች አስተዳደር ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ፤ ኤጀንሲው ያሉትን ቤቶች ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ፍትሃዊነት በሰፈነበት ሁኔታ እንዲያስተዳድር የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲን ለማቋቋም በወጣ አዋጅ ቁጥር 555/2000 አንቀጽ 11(2) መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡