በሀገራችን ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት የተሰጠ መሆኑና የመምህራን ትምህርት ደረጃና ብቃት ቁልፍ በመሆኑ ለዘላቂና ሁለንተናዊ ልማት መረጋገጥ አስተዋጽዖ ማድረግ ይቻል ዘንድ የከፍተኛ ትምህርት የትምህርት እድል አሰጣጥን በስርዓት በመምራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ሰልጣኞችን አቅም መገንባት መንግሥት በጽኑ የሚያምን በመሆኑ፤
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት እድል አሰጣጥን ውጤታማ ለማድረግ ወጥ፤ ግልፅ፤ ፍትሃዊ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፤
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሌሎች ተቋማት ብቁና በቂ የሰው ኃይልን ለማፍራት አማራጭ ስኮላርሽፕ ፕሮግራሞችን በማበረታታት የመንግሥትን በጀት እና ወጪ መቀነስ በማስፈለጉ፤
በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች እና ሌሎች ተቋማት የተናበበ ስርዓት በመዘርጋት፣ በመምራትና በማስተዳደር ውጤታማ የሆነ የከፍተኛ ትምህርት የትምህርት እድል አሰጣጥን ለመተግበር በሁሉም ደረጃ ተዓማኝነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ስርዓት እንዲኖር በማስፈለጉ፣
የትምህርት ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 1152/2011 አንቀጽ 86(5) በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ተቋማት የተሟላ ነጻነት እስኪጎናፀፉ ድረስ ይህንን ለመንግሥትና ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚ ሰራተኞች፣ ለሌሎች ተቋማት ሰራተኞች እና ለበትረ ሳይንስ ተማሪዎች የሚሰጥ የስኮላርሺፕ ማስፈጸሚያ መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡