የሀገራችንን የታሪክና የባህል ቅርሶችን በመንከባከብ፣ ሊደርስባቸው ከሚችሉ አደጋዎች በመጠበቅ፤ ጉዳት የደረሰባቸውን በመጠገንና በመንከባከብ ለቅርሱ ባለቤቶች፣ ለቅርሱ አካባቢ ማኅበረሰብና ብሎም ለመላ ሀገሪቱ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታን እየሰጡ ወደ መጪው ትውልድ እንዲተላለፉ ለማስቻል፣
የታሪክና የባህል ቅርሶች በአያያዝ፤በአጠቃቀም እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መንስኤ ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ፣
በቅርሶች ላይ የሚደርሰውን ብልሽት ማቆም የማይቻል ሲሆን፣ የጉዳቱን መጠንና ፍጥነት ለመቀነስ ታሪካዊ ይዘቱ ሳይለውጥ እና የቅርስ እሴታቸው ሳይሸራረፍ በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ እንደ ጉዳቱ መጠን
እርምጃዎችን በተገቢው ጊዜና ወቅት መውሰድ አስፈላጊ በመሆኑ፣
ዓለም አቀፉን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መርህዎችንና ስታንዳርዶችን መሠረት በማድረግ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ ሁኔታ የቅርስ ጥበቃ፣ እንክብካቤና ጥገና ተግባራትን መምራት በማስፈለጉ፣
የቅርስ ጥበቃ፣እንክብካቤና ጥገና ተግባርን ብቃት ባላቸው ባለሞያዎች የቅርሶችን እሴት ዘለቄታዊነት በጠበቀ መልኩ በተመጣጠኝ ወጪና በጥራት በማከናወን የቅርሶችን ሕልውና ለማረጋገጥ፣
በተጨማሪም ከባለስልጣኑ ጋር በመተባበር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ተግባርለሚያከናውኑ የቅርስ ባለቤቶች፣ ክልሎች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ማኅበራት እና በዘርፉ የተሰማሩ ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና ባለሙያዎች መብትና ግዴታ በግልፅ ማስቀመጡ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ አዋጅ 209/1992፣ አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡