ስፖርት ማንኛውም ግለሰብ ዕድሜና ጾታ ሳይገድበው ጤንነቱን ለመጠበቅ ለመዝናናት አካልን ለመገንባትና አእምሮውን ለማበልፀግ እንዲሁም አቅሙንና ችሎታውን ለመመዘን በግል ወይም በጋራ በተደራጀና ባሌተደራጀ መልክ በማንኛውም ጊዜና ቦታ የሚከናወነውን የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያጠቃልላል፡ ፡ ስፖርት ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ወሳኝ ከሆኑት ዘርፎች አንዱ ሲሆን በተለይም ከመዝናኛነቱ ባለፈ ጤናማና ምርትማ ዜጋ ለማፍራት ወሳኝ ነው፡ ፡
ስለሆነም ስፖርት ለልማትና ለሰላም ማበርከት ያለበትን አሰተዋፆ እንዲያበረክት እነዲሁም ለማኅበራዊና ለኢኮኖሚዊ ልማት የሚኖረው ፋይዳ ለማሳደግ የመንግሥት፣ የህብረተሰቡንና የባለሃብቱን ተሣትፎ በየደረጃው ማሳደግ ተገቢ ይሆናል፡ ፡ በመሆኑም ባለሃብቱ እና የስፖርት ባለሙያ መስክ የሚኖረውን ድርሻ እንዲወጣ ግልጽና የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ከመንግሥት አስፈፃሚ አካላት የሚጠበቅ መሆኑን በማመን መንግሥት የሀገራችን የንግድ አሠራር ከመሠረቱ በመለወጥ ልማትን ለማፋጠን በዘረጋው አዲስ የአሠራር ስርዓት መሠረት በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 በአንቀጽ 30/31 ስር አዋጅ በሚሸፍናቸው የንግድ ስራዎች ለሚሰጡ ፈቃዶች ሊሟሉ የሚገባቸውን የሙያ ብቃት መስፈርቶች አግባብነት ያላቸው የሴክተር መስሪያ ቤቶች በመመሪያ እንዲወስኑ በደነገገው መሠረት ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በ2003 ዓ.ም የስፖርት ነክ የንግድ ስራ የሙያ ብቃት መስፈርት መመሪያ አውጥቶ ሲሰራበት ቆይቷል፡ ፡
በመሆኑም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባ ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 በአንቀጽ 41 በንዑስ አንቀጽ 1 የተሻሻሉትን በማካተት የተለያዩ የኮድ ማስተካከያዎች በመደረጉ አዲስ ፈቃድ መስጫ መደብ በመጨመሩ እንዲሁም በአሠራር ወቅት የታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር መመሪያውን በ2011 ዓ.ም በማሻሻል ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡ ፡
ይሁን እንጂ የኢ.ፌ.ዲ.ሪን ግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለሁለተኛ ጊዜ የተሻሻለውን የንግድ ስራ ፈቃድ መስጫ መደቦች ክለሳ በማድረጉ ይህንን መሠረት በማድረግ ይህን መመሪያ ለሁለተኛ ጊዜ በ2012 ዓ.ም አሻሽሎ አውጥቷል፡ ፡