የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚተዳደሩበት አዋጅ ቁጥር 25/1984 የመንግሥት ትርፍ ድርሻ ክፍያን በተመለከተ ማንኛውም የመንግሥት የልማት ድርጅት በየበጀት ዓመቱ ከሚያስመዘግበው የተጣራ ትርፍ ላይ ህጉ በሚፈቅደው መሠረት የመጠባበቂያ ሃሳብ (Legal Reserve) ከተነሳ በኋላ ከባለሥልጣኑ ጋር በመመካከር የሚወስነውን የመንግሥት ትርፍ ድርሻ የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በሰባት ወራት ውስጥ ገቢ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
ይሁን እንጂ በሂደት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 107/1996 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የልማት ድርጅቶች የተጣራ ትርፋቸውን በሙሉ ለመንግሥት (60% የትርፍ ድርሻ ክፍያ፣ 40% የኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ) እንዲያስገቡ በማስቀመጡ እንቅስቃሴያቸውን በብድር ብቻ እንዲያስኬዱ የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጥሮ በመቆየቱ የፋይናንስ ሁኔታቸው አሣሣቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህንን በመገንዘብ የትርፍ ድርሻ አከፋፈሉ የድርጅቶችን ቀጣይነት በሚያረጋግጥ አካኋን እንዲሆን መነሻ ጥናት ተካሂዶ ለገንዘብ ሚኒስቴር ቀርቦ እንዲጸድቅ ተደርጓል፡፡
በጸደቀው የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ፖሊሲ ድርጅቶች በየአመቱ ከሚያገኙት የተጣራ ትርፍ ህጉ በሚፈቅደው መሠረት የመጠባበቂያ ሂሳብ (Legal Reserve) ካስቀሩ በኋላ ከሚተርፈው የገንዘብ መጠን 60 በመቶ ለመንግሥት የትርፍ ድርሻ ገቢ እንዲያደርጉ እና ቀሪውን 40 በመቶ ደግሞ በኤጀንሲው በሚዘረጋው ሥርዓት መሠረት ጥቅም ላይማዋል እንዲቻል ወስኗል፡፡
በመሆኑም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የልማት ድርጅቶች ሊጠቀሙበት የሚችሉትን ቀሪ የትርፍ ድርሻ በምን የአሠራር ሥርዓት ማስተዳደር እንደሚገባ ግልፅ መመሪያ ማዘጋጀቱ ተገቢ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በዚህ መመሪያ መሠረት ለልማት ድርጅቶች እየተፈቀደ የሚቀረው ትርፍ ለምን ዓላማ፣ በምን ሁኔታ፣ በምን የቁጥጥርና ክትትል አሠራር ሥራ ላይ እንደሚውልና ውጤታማ ስለመሆኑም በየጊዜው ክትትል እንዲደረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የኤጀንሲውን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው ደንብ ቁጥር 445/2011 አንቀጽ (5) ንዑስ አንቀጽ (3) እና (8) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ኤጀንሲው ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡