የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሥራ አመራር ቦርድ ግምገማ ተለዋዋጭ ከሆነው የዓለም አቀፍ የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ ውስጥ ውጤታማ ሆኖ ለመገኘት ቅድሚያ ትኩረት ከሚሰጣቸው የኮርፖሬት ገቨርናንስ ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡፡
በመሆኑም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በአዋጅ ቀጥር 25/84 እና በኮርፖሬት ገቨርናንስ ኮድ መሠረት የቦርድ ስራ አመራሮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ግልጽ፣ አሳታፊ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን የሚያደርግ የግምገማ ስርዓት እንዲኖር ማድረግና የኮርፖሬት ገቨርናስ ክፍተቶችን በወቅቱ ለይቶ አስፈላጊ የዕርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲቻል፤
ቦርድ በጋራ እና እንደ ግለሰብ ያላቸውን አፈጻጸም በመገምገም የክህሎት፣ የዕውቀት ወይም የትኩረት ጉድለቶችን ለይቶ በማወቅ ተመጣጣኝ የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ለማረጋገጥ፤
ቦርዶች የሚመሩት የመንግሥት የልማት ድርጅት ውጤታማ፣ ምርታማ፣ ተወዳዳሪና አትራፊ እንዲሆን ለማስቻል የሚረዳና እሴት የሚጨምር አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ለማረጋገጥ፤
በተጨማሪም ቦርድና የቦርድ ንኡሳን ኮሚቴዎች የቡድንና የተናጠል እንቅስቃሴ መናበብና ተግባቦት፣ የመረጃ ልውውጥ ሂደት እና የኮርፖሬት ገቨርናንስ ፖሊሲዎች ተግባራዊነት በድርጅቱ ያመጣውን ተጽእኖ በመገምገም ቦርድ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ማስቻልና የአፈጻጸም ውጤት ማስቀመጥ በማስፈለጉ፤
በሚመራቸው ድርጅት ቦርድ በራሡም ሆነ በማኔጅመንት ላይ በውጤትና ውጤታማት ላይየተመሠረተ የተጠያቂነትና የዕውቅና ሥርዓት በጥብቅ ዲሲፒሊን እያሰፈነ መሆኑን ለማረጋገጥ፤
ከላይ የተገለጹትን ዝርዝር ዓላማዎች ለማሳካት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የኤጀንሲውን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው ደንብ ቁጥር 445/2011 አንቀጽ (5) ንዑስ አንቀጽ (3) እና (4) መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡