የበጎ አድራጎት ኮሚቴን በማቋቋም ከለጋሾች አስፈላጊውን ንብረት ወይም ገንዘብበማሰባሰብ እንደ ረሃብ፣ ድርቅ፣ ጦርነት፣ የአንበጣ መንጋ፣ ጐርፍ፣ የእሣት ቃጠሎ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የእሣተ ገሞራ መፈንዳት፣ የበሽታ ወረርሺኝ እና የመሣሠሉት ሰው ሰራሽ ወይም የተፈጥሮ አደጋዎችን በመከላከል፣ በመቀነስና በማስወገድ ሕብረተሰቡን ከሚደርስበት ጉዳት ለመታደግ፤ ጉዳት የደረሰበት የሕብረተሰብ ክፍል ካለም አስፈላጊው ሰብዓዊ ዕርዳታ ተደርጐለት ወደ ተረጋጋ የቀድሞ ሕይወቱ እንዲመለስ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን መደገፍ፣ ማበረታታትና ለሥራቸውም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን በመጠቀም እንዲሁም ሕጋዊ ሰውነት ያላቸውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ማቋቋም ሳያስፈልጋቸው የበጎ አድራጎት ኮሚቴን በማቋቋም ብቻ ከለጋሾች አስፈላጊውን ዕውቀት፣ ገንዘብና ንብረት በማሰባሰብ የፈለጉትን የበጎ አድራጎት ሥራ ማከናወን ለሚፈልጉ ስዎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
ከለጋሾች የሚሰበሰበው ገንዘብና ንብረት መጠንና አጠቃቀሙን ለመቆጣጠር፤ እንዲሁም ለታለመለት የበጐ አድራጐት ሥራ የዋለ መሆኑን ለማረጋገጥ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኀበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀጽ 50(3) እና በበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኀበራት የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀጽ 15(1) (ሠ) በተሠጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡