በሆስፒታሎች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃውን የጠበቀና በሥርዓት የሚመራ እንዲሆን ለማስቻል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል ሆስፒታሎች አስተዳደር ደንብ ቁጥር 167/2001 ማጽደቁ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ደንብ ይበልጥ ለማብራራትና ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲረዳ በማሰብ የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመንግሥት ሆስፒታሎች የግል ህክምና ክፍል አገልግሎት የአሠራርና የአደረጃጀት መመሪያ ቁጥር 001/2002 ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
የዚህ አገልግሎት መጀመር የባለሙያዎችን የስራ ተነሳሽነት በመጨመርና ባሉበት ሆስፒታል ረጅም ጊዜ ቆይተው እንዲያገለግሉ ከማስቻሉም በላይ ለህብረተሰቡ አማራጭ የህክምና አገልግሎት ሆኗል፡፡ይሁን እንጂ በአሠራሩ ላይ በተደረጉ ጥናቶች የአላቂ እቃዎች ለሆስፒታሉ የሚመለስበት ሥርዓት አለመኖር፣ የግል ህክምና አገልግሎት በመደበኛ የህክምና አገልግሎት ሰዓት መጀመር፣ የስው ሃይል አመዳደብ መርሆ አለመኖር፣ የአገልግሎት ዋጋ ወጥ ያለመሆን፣ የገቢ ትርፍ ክፍፍል ሥርዓት አለመኖር እና የመሳሰሉት ችግሮች የተስተዋሉ በመሆኑና ከተጠቃሚው ህብረተሰብ በሚነሱ ጥያቄዎች መሠረት ከዚህ በፊት በወጣው መመሪያው ያልተሸፈኑ ሁኔታዎችን ለማብራራትና የዋጋ ትመና ጣሪያ ለማስቀመጥ መመሪያውን ማሻሻል በማስፈለጉ ከሆስፒታል ሃላፊዎች እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይህ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 167/2001 ለጤና ጥበቃ ሚኒስተር በተሰጠው ሥልጣን የፌዴራል ሆስፒታሎች የግል ህክምና ክፍል የአፈጻጸም መመሪያ ወጥቷል፡፡