የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራትን ለመመዝገብና ለማስተዳደር በወጣው አዋጅ 621/2001 እና በደንብ ቁጥር 168/2001 መሠረት ሕብረተሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር በሕግ አግባብ ሲፈርስ ወይም በተለያየ ምክንያት ድርጅቱ የማይጠቀምበት ንብረት ሆኖ ሲገኝ በሕዝብ ስም ያሰባሰበው ሃብትና ንብረት በድርጅቱ ጥያቄ ወይም በኤጀንሲው ውሳኔ ለተመሳሳይ ዓላማ ማዋል እንዲቻል ንብረቱን ለማጣራት፣ ለማስተላለፍ እና ለማስወገድ የሚረዳ ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ፡፡
በሕግ ያልፈረሱና በሥራ ላይ ያሉ በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለረጅም ጊዜ የተገለገሉባቸውና በእርጅና ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ ወይም ጊዜያቸው በማለፉ ምክንያት የማይፈለጉ ዕቃዎችን ለማስወገድ ለኤጀንሲው የሚያቀርቡት የይወገድልን ጥያቄን ለማስተናገድ እንዲቻል ዝርዝር የማስፈፀሚያ ስርዓት ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ፡
በሌላ በኩል የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር በተጠቃሚው ሕዝብ ስም ከቀረጥ ነፃ የገቡና የኮድ 35 አገልግሎት ሽፋን የተሰጣቸው ተሸከርካሪዎችን ስርዓት ባለው መንገድ ለማስተዳደር፣ለማጣራት፣ለማስተላለፍ እና ለማስወገድ ይቻል ዘንድ ግልፅ መመሪያ መኖሩ አስፈላጊ በመሆኑ፡፡
የኢፌድሪ በጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራትን ለመመዝገብና ለማስተዳደር በወጣው አዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀጽ 9/4/ መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡