መንግሥት በፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ የሀገራችንና የውጭ ባለሀብቶች በቱሪዝም ዘርፍ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ የሚገኝ ከመሆኑ የተነሳ፣ በሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ የጉዞ ወኪልና አስጎብኝ ድርጅት የንግድ ዘርፎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባለሀብቶች መሰማራታቸውን ተከትሎ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እጥረት በመስተዋሉ፣
የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች ቀጥረው ለማሰራት የሚፈልጓቸው የውጭ ባለሙያዎች የዜጎችን የሥራ ዕድል የማይሻማ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ከፍተኛ ክህሎትና ልምድ ያላቸው የውጭ ባለሙያዎች በተመረጡ የሙያ መስኮች እንዲሰማሩ ትብብር በማድረግ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት ለዜጎች እንዲያስተላልፉ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣
ለተገልጋዮች ግልጽ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 916/2008 አንቀጽ 35 የተሰጡትን ተግባርና ኃላፊነቶች በአግባቡ ለመፈጸም እንዲያስችል ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡