አገሪቷ ላለፉት አሥር ተከታታይ ዓመታት እያስመዘገበች ባለዉ ፈጣን ዕድገት፣በተፈጠረው የኢኮኖሚ መነቃቃት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ ወደ ዉጭ የሚላኩ ዕቃዎች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡ ይኽም ዕድገት ወደ ፊት በእጥፍ እንደሚያድግ ይገመታል፡፡
በአንፃሩ ዕቃን ከባሕር ወደብ የማንሳት አቅማችን በዚያው መጠን ባለማደጉ እና ከአስመጪው ጀምሮ በሃደቱ ተዋናይ በሆኑ አካላት ላይ ከሚታዩ ድክመቶችና ችግሮች፤ የማጓጓዝ ሥርዓቱ ፈጣን አለመሆኑ ፤በአገር ዉስጥ በቂ የማከማቻ መጋዘን አለመኖሩ! የገቢ ንግድ ዕቃዎቻችን በዉጭ ምንዛሪ ለሚከፈል ከፍተኛ የመጋዘን ኪራይ እና ዲመሬጅ /Demurrage/ እንዲሁም ከቆይታ ብዛት ለብልሽት ከመጋለጣቸዉም በላይ ለባሕር ወደብ መጨናነቅ፣ አስመጪዎች ዕቃቸውን በወቅቱ በዉላቸዉ መሠረት ማንሳት ባለመቻላቸው እና ዕቃዎች በተገቢ ጊዜ አገር ዉስጥ ባለመግባታቸዉ ሳቢያ በአገር ውስጥ የዕቃዎች እጥረት መከሰት፤ በዕቃ እጥረቱ ምክንያት የሚፈጠር የዋጋ ዉድነት፣የፋብሪካ ምርቶች መቋረጥ፤ የግንባታዎች መዘግየት እንዲሁም ለልዩ ልዩ አላስፈላጊ ወጪዎችና መሰል ጉዳቶች እንዲከሰቱ ምክንያት ከመሆን በዘለለ ዕቃዎች በባህር ወደብ ላይ ከ6 ወር በላይ በመቆየታቸው በወደብ ባለቤት አገር ተወርሰው በጨረታ የመሸጥ ሁኔታ የሚደጋገም ክስተት የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ መሠረት ከላይ ለተጠቀሱትን ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ እና የሚመለከታቸው አካላት እስካሁን ተግባራዊ ሲያደርጉት የቆዩት ተግባርና ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨማሪ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነቶችና ግዴታዎች ለመወሰን በማሪታይም ዘርፍ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 549/1999 አንቀጽ 18 (ለ) መሠረት ለትራንስፖርት ሚኒስቴር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህ ረቂቅ መመሪያ ተዘገጅቷል፡፡
ይህ የአሠራር ሥርዓት ሥራ ላይ የሚውለው፣ ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በተጨማሪ የሌሎች የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ተግባር እና ኃላፊነት ኃላፊነት ለመወሰን እንዲቻል እንዲሁም ሥርዓቱ ከመልቲ ሞዳል አዋጅ ጋር የተጣጣመ ለማድረግ የመልቲ ሞዳል አዋጅ ቁጥር 548/1999፣ የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 549/1999፤ የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ 622/2001 የደረቅ ወደብ ለባለዕቃዉ ስለሚኖረዉ ኃላፊነት ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር 588/2002 በባንክ በመያዣነት ስለተያዙ የማይንቀሳቀሱ እና የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች የወጣ አዋጅ ቁጥር 97/1990 እና ማሻሻያዎቹ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ የገቢ እቃዎችን የትራንዚት ጊዜ እና ወጪ ኢኮኖሚያዊነት ለማረጋገጥ ወደ ደረቅ ወደብ ተርሚናል የሚገቡ ዕቃዎችን በተቻለ ፍጥነት እየወጡ ለሌሎች ተተኪ ገቢ ዕቃዎች ቦታ እንዲለቁ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎችና ደንቦችን በማይቃረን ሁኔታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡