የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባላቸው ሚና ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ አካባቢያዊ እንዲሁም የሠራተኛውንና የማህበረሰቡን ጤንነትና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ፤
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ዓላማቸውን ለማሳካት ከሚያደርጉት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጐን ለጐን የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሥራቸው አንድ አካል አድርገው ሲወስዱና ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ሲፈጥሩ ለህልውናቸው ዋስትና አንዱ ማረጋገጫ በመሆኑ፤
በአሁኑ ወቅት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የተለያዩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ቢሆንም ማኅበራዊ ኃላፊነት አገልግሎት አሰጣጥ የሚመራበት ወጥነት ያለው አሠራር መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤
በሌላ በኩል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሊባል በሚችል ሁኔታ ተገቢውን ማኅበራዊ ኃላፊነት አገልግሎት የሚሰጡ የልማት ድርጅቶች የፍትሃዊነት አሠራር ስርዓት መተግበራቸው አንዱ ማሳያ ተደርጎ ስለሚወሰድ፤
በዚህም መሠረት የማኅበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለምአቀፍ ግዴታ እየሆነ የመጣና ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ የሚያደርጉ የልማት ድርጅቶች በማህበረሰቡ ያላቸውን ተቀባይነት የሚያጠናክር በመሆኑ፤
ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የማኅበራዊ ኃላፊነት አገልግሎት አሰጣጥ በልማት ድርጅቶች ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ የልማት ድርጅቶችን ተጠቃሚነት የሚያጠናክር በመሆኑ፤
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኤጀንሲውን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው ደንብ ቁጥር 445/2011 አንቀጽ (5) ንዑስ አንቀጽ (3) መሠረት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚመራበትን ይህንን የኮርፖሬት የማኅበራዊ ኃላፊነት አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ አውጥቷል፡፡