በከተማችን የመንገድ ትራፊክ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን መንገዶችን በጊዜያዊነት ዘግቶ መጠቀም እና የመንገድ ላይ ኩነት ፍላጎቶች በዚያው መጠን እያደጉ በመምጣታቸው የትራፊክ ፍሰትን በማስተጓጎል ለትራፊክ አደጋ መፈጠር መንስኤ ስለሆኑ እነዚህን የመንገድ ላይ ኩነቶች በመቆጣጠርና ስርዓት በማስያዝ በመንገድ ተጠቃሚው ዘንድ ተቀባይነት ያለው የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ለማድረግ ኤጀንሲው በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ በመሆኑ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ መንገድ ለመዝጋትና ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን ወይም ከታለመለት ዓላማ ውጪ ለመጠቀም ለሚቀርብ ጥያቄ ፈቃድ እንዲሰጥ፣ እንዲያድስ፣ የመንገድ ላይ ኩነቶችን እንዲያስተዳድር እንዲሁም ሕግን በሚተላለፉ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ወይም አንዲወሰድ እንዲያደርግ የከተማ አስተዳደሩን አስፈፃሚ አካላት እንደገና ለማደራጀት በወጣው በአዋጅ ቁጥር 64/2011 አንቀጽ 49 (10) ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ፤
ይህንን ጥረት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ኤጀንሲው የሚመራበት የአሠራር መመሪያ ባለመኖሩ መንገድን በጊዜያዊነት ዘግቶ ለመጠቀምና የመንገድ ላይ ኩነቶች የሚስተናገዱበት የአሠራር ስራዓት ወጥነት እንዲኖረው መመሪያ መምራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ አስተዳደሩን አስፈፃሚ አካላት እንደገና ለማደራጀት እና ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው በአዋጅ ቁጥር 64/2011 አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 3(ሠ) መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥጧል፡