የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንብረት የሆኑትን የመንግሥት የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ትክክለኛ መረጃዎችን በማደራጀት፣ በተገቢዉ በማስተዳደር ዝቅተኛ ገቢ ያለዉ የህብረተሰብ ክፍል፣ወጣቶችን፣ሴቶችንና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉን የአካል ጉዳተኞችን የቤት አስተዳደር ስርዓቱ ይበልጥ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የአሠራርሥርዓት መፍጠር በማስፈለጉ፣
የከተማዉ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግርለማቃለል የመንግሥት ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች፣ በባለሀብቶች፣ በህብረተሰቡ እና የበጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የተገነቡ ለኪራይ የሚዉሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተዳደር የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች በመልሶ ማልማት፣በተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ አደጋ ለሚነሱ ተነሺዎች ምትክ ስለሚሰጥበት ሁኔታ አሠራር መዘርጋት በማስፈለጉ፤
የአስተዳደሩ ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አያያዝ እና አጠባበቅ ሁኔታ ለክትትልና ቁጥጥር አመቺ እንዲሆን በማድረግ በየጊዜዉ እየጨመረ የመጣዉን የመንግሥት ቤቶችን ያለአግባብ መጠቀምና ወደግል ይዞታ የማዞር ህገወጥ ተግባራትን በመግታት የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፣
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የከተማ አስተዳደሩን አስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 74/2014 አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 3 እና በደንብ ቁጥር 11/1996 መሠረት ይህንን መመሪያ አዉጥቷል፡፡