የዓለም አቀፉ ሚዲያና ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶችና ባህላዊ እሴቶች፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች በትክክል ተገንዝቦ ለውጭው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙሃን ወኪሎችና የፊልም ቀራጮች ጉልህ ሚና የሚጫወቱ በመሆኑ፤ እንዲሁም የአገሪቱን ጥቅምና ሉአላዊነት ያከበረ የዜና ዘገባና የፊልም ቀረጻ ስራ መስፋፋቱ ለአገሪቱ በጎ ገጽታ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ፤
በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 6(14) መሠረት የውጭ ሀገርመገናኛ ብዙሃን እና የዜና ወኪሎች በአገራችን ለመንቀሳቀስ በቅድሚያ መመዝገብ ያለባቸው በመሆኑ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ተራኪ ወይም ዘጋቢ ፊልም ለማንሳት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 66/1992 አንቀጽ 5 መሠረት ፈቃድ ማግኘት የሚያስፈልግ በመሆኑ፤ ግልጽ፣ ቀልጣፋ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት የምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት ለመዘርጋት፤
የቀድሞ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መታጠፍን ተከትሎ ከጠቅላይሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በቁጥር መ10-11/830/1 ጥቅምት 15 ቀን 2011ዓ.ም. በተላለፈው ሰርኩላር የዘጋቢ ወይም ተራኪ ፊልም የፈቃድ አሰጣጥ ስራ ወደ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ተላልፎ እንዲሰራ በመወሰኑ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 66/1992 አንቀጽ 13 እና በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር1238/2013 አንቀጽ 90(2) መሠረት ይህ መመሪያ በባለስልጣኑ ቦርድ ወጥቷል፡፡