እያደገ የመጣውን የአርሶ አደሩን የማዳበሪያ ፍላጎት ለማሟላት ማዳበሪያ በየአመቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ተገዝቶ እየገባ ሲሆን በአገር ውስጥ የማሰራጨት ስራም ከፍተኛ ገንዘብ፣ የሰው ኃይል፣ የማከማቻ አቅምና ልምድ የሚጠይቅ ነው፡፡ የፍላጎት ዳሰሳ ችግር፣ የዓለም የማዳበሪያ መግዣ ዋጋ መናር : የአገር ውስጥ ማጓጓዣና የሌሎች ወጭዎች ጭማሪ በማሳየታቸው ለአርሶ አደሩ በችርቻሮ የሚሽጥበት ዋጋ በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡
ይህ አዝማሚያ በዓለም የምርቶች ዋጋ መለዋወጥ ምክንያት እየቀጠለ የሚሄድ ከሆነ የአርሶ አደሮችን አቅም በመፈታተን በማዳበሪያ አጠቃቀም ብሎም በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ ነው፡፡
አርሶ አደሩ ማዳበሪያን በወቅቱ፣ በሚፈልገው ጥራት፤መጠንና በተወዳዳሪ ዋጋ አግኝቶና ተጠቅሞ ምርታማነቱን ለማሳደግ እንዲችል የአቅርቦት ስርዓቱን የሚያቀላጥፍና ወጭን የሚቆጥብ የአሠራር መመሪያ መቀየስና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በመሆኑም ከማዳበሪያ ፍላጎት ዳሰሳ ጀምሮ ተጠቃሚው አርሶ አደሩ ዘንድ እስከሚደርስ ድረስ የሚኖሩ የአቅርቦት እንቅስቃሴዎችንና ተግባራትን ከግምት በማስገባት እንዲሁም ዘመናዊና ቀልጠፋ የአሠራር ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል ይህ የማዳበሪያ ፍላጎት ዳሰሳ፣ ግዥ፣ አቅርቦትና ስርጭት መመሪያ የኢትዮዽያ ፌደራላዊ ዲሞከራሲያዊ ሪፐብሊክ የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር 916/2008 ዓ/ም አንቀጽ 09 ንዑስ አንቀጽ ረ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህ መመሪያ ወጥቷል፡፡