በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 36(1)(ሐ) መሠረት ሕፃናት ከወላጆቻቸው ማግኘት በተለይም የእናት የእናት ጡት ወተት የማግኘት መብታቸውን ለማረጋገጥ ወላድ ሴት መንግሥት ልጆቻቸውን በሚሰሩበት አካባቢ የሚያቆዩበትና ጡት የሚያጠቡበት ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፣
ሴት የመንግሥት ሰራተኞች በመውለዳቸው ምክንያት በስራቸው ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ ይፈጠርባቸው የነበረውን እንቅፋቶች በማስወገድ ያለምንም ስጋትና ሃሳብ ሙሉ ኃይላቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ተጠቅመው ውጤትእንዲያስመዘግቡ ለማድረግ፣
ሴት የመንግሥት ሰራተኞች ትውልድን የመተካት ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ህጻን ልጃቸውን ለመንከባከብ በሚል ስራ የሚያቋርጡበት አጋጣሚዎች እየጨመረ በመምጣቱ በመንግሥት መ/ቤቶች ህጻናት ልጆቻቸውን ማቆየት የሚችሉበትን ቦታ በማመቻቸት የስራ ዋስትናቸውን እንዳያጡ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፣
የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ተሻሽሎ በወጣው የፌዴራል የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 48(6) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡