የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 ስር የተቀመጡት የፍትሐብሔር ኃላፊነቶች አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓትን የሚደግፍ በመሆኑ፣
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፌዴራል መንግስቱ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን አለመግባባት የሚፈቱበትን መንገድ እንደሚወስን በመቀመጡ፣
ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የግልግል ዳኝነት ጥያቄ በስፋት እየቀረበ የመጣ በመሆኑ፣
የመንግሥት ተቋማት በሚገቧቸው ውሎች አማካኝነት የሚፈጠርን አለመግባባት ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ በመፍታት የሕዝብና የመንግሥትን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ የተቋሙ ኃላፊነት በመሆኑ፤
በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በፍትሐብሔር ጉዳዮች የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መፍታት መልካም ግንኙነትን የሚጠብቅ፣ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታና
ሀገራዊ ልማትን የሚደግፍ በመሆኑ፣
በመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ (BPR) ጥናት ላይ እንደተመለከተው በመንግሥት ተቋማት መካከል የሚፈጠር የፍትሐብሔር አለመግባባት 1ዐዐ% እንዲሁም ከሌሎች አካላት ጋር የሚኖራቸውን የፍትሐብሔር አለመግባባት 85% በአማራጭ የሙግት መፍቻ ለመፍታት እንዲቻል የአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች አሠራር በዋናው መሥሪያ ቤት፣ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና በምድብ ፅ/ቤቶች ደረጃ ወጥነት ባለው መልኩ መዘርጋት የሚያስፈልግ በመሆኑ፣
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 21(2) መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡