አገራችን ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ አመታት በማስመዝገብ ላይ ያለችውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ መንግሥት ካስቀመጣቸው ግቦች መካከል የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማሳደግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ለዚሁም ግብ ስኬት ወሳኝ ሚና የሚኖረውን የወጪ ንግድን ማሳደግ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው በአብዛኛው የግብርና ምርቶች ሲሆኑ መጠናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ የኤክስፖርት ንግሳችን ከዚህም ሰፋ ብሎ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን ጨምሮ እያደገ እንደሚሄድ የሚጠበቅ ሲሆን ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ቀጣይነት ለማስጠበቅ እና ዘርፉን ለማሳደግ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አሠራራቸውን እቀናጅተው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ዘላቂ የክትትልና የድጋፍ ማዕቀፍ ቀርጸው መንቀሳቀስ የሚኖርባቸው ሲሆን ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በአሠራር ላይ የሚታዩ ችግሮችን በወቅቱ ለመፍታት የየበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡
በመሆኑም የአገራችንን የውጭ ንግድ ልማት ለመደገፍ መከናወን ካለባቸው ቁልፍ ተግባራት ውስጥ አንዱ የትራንዚት ወጪና ጊዜን ለመቀነስ የሚያስችል የትራንዚት ሥርዓት መመሪያ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የአገሪቱ የወጪ ንግድ በተፈላጊ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ የተረጋገጠ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀልጣፋ የወደብና የትራንዚት አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል የአሠራር መመሪያ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ መስኩ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነቱ እንዲረጋገጥ የሚመለከታቸው አካላት የተቀናጀ እና የተሳለጠ የአሠራር ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል፡፡
በዚህ ሂደት ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል በወጪ ዕቃዎች የትራንዚት ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት በዘላቂነት ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባ የትራንዚት ትራንስፖርት አገልግሎት የሚመራበትን ሥርዓት የመዘርጋት አስፈላጊነት ታምኖበታል፡፡ የትራንዚት ትራንስፖርት ሥርዓቱ መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ወሣኝ የሆኑና በትራንዚት ትራንስፖርት ሂደቱ እያጋጠሙ ያሉትን በቀጣይም ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ግምት ውስጥ ያስገባ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስያዝ የግድ ይላል፡፡
በዚህ መሠረት የወጪ ደረቅ ዕቃዎች የትራንዚት ሥርዓት የሚመራበትን አሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እና የሚመለከታቸው አካላት እስካሁን ተግባራዊ እያደረጉ የቆዩት ተግባርና ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የወጪ ንግድ ልማት መስኩ የታለመለትን ዓላማ ያሳካ ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነቶችና ግዴታዎች ለመወሰን በማሪታይም ዘርፍ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 549/1999 አንቀጽ 18 (ለ) ለሚኒስቴሩ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህ መመሪያ ወጥቷል፡፡