በኢትዮጵያ ፈጣን የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ የከተማ ነዋሪዎችንና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማጠናከር መልካም ተሞክሮዎችንና ልምዶችን በማስፋፋት የከተማ ልማት ፖሊሲውን እና የከተማ ልማት ፕሮግራሞችን ትግበራና ስኬት ማፋጠን ይቻል ዘንድ ዓመታዊ የከተሞች ቀን፣ ሳምንትና ፎረም በመባል ተሰይሞ በተለያዩ ከተሞች አስተናጋጅነት በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር የቆየ እና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ በመሆኑ፣
ወደፊትም በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደዉ የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም ኤግዚቢሽን በተደራጀና ወጥ በሆነ ሁኔታ ከዝግጅት እስከ ፍፃሜ እንዲቀጥል ለማድረግ እስከ 7ኛው የከተሞች ፎረም ድረስ የተገኙ ተሞክሮዎች እና በHabitat አማካኝነት የአለም የከተሞች ፎረም የኤግዚቢሽን ዝግጅት ልምዶችን በማካተት አጠቃላይ አቅጣጫ እና የትኩረት መስኮች በሚያመላክት መልኩ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣
በኤግዚቢሽን ዝግጅቱ ከተሞች በዋና ዋና የከተማ አጀንዳዎች ዙሪያ በእድገት ጎዳና ለለውጥ እያደረጉት ስላለው ጥረት፣ ስላስመዘገቧቸው ስኬቶች፣ ስለገጠሟቸው ተግዳሮቶች እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በተሞክሮነት ሊወሰዱ የሚችሉ ስራዎቻቸውን ማራኪና በቀላሉ መልዕክት ማስተላለፍ በሚችል አቀራረብ ለሕዝብ ክፍት በማድረግ መደበኛ ያልሆኑ የእርስ በርስ ውይይቶች መነሻ ነጥብ እንዲሆን በማስቻል የእውቀት ልውውጥ የሚፈጠርበት በመሆኑ፣
ይህን ለማድረግም የኤግዚቢሽን ዝግጅቱና አቀራረቡ ከዚህ በፊት ይካሄድበት ከነበረበት አካሄድ ለውጥ በማድረግ በተረጋጋ ሁኔታ መረጃ በሚሰጥና መልእክት በሚያስተላልፉ የተለያዩ ፎቶግራፎች፣ ስታንዶች፣ ዶክመንተሪዎች እና መሰል የማቅረቢያ ዘዴዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት በማስፈለጉ፣ እና የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ኤግዚቢሽንን በሚመለከት ለተሳታፊ ከተሞች ጠቃሚ መረጃ በመስጠት፤ የአዘጋጆችን፣ የተባባሪዎችን እንዲሁም የተሳታፊዎችን ሚና በመለየት በየሁለት ዓመቱ በሚመረጠዉ ከተማ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የኤግዚቢሽን ሥራ የሚመራበትን ስርዓት ለመደንገግ ይህ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡