የመንገድ ትራፊክ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በተለይ የእግረኞች ተጋላጭነትን አስከፊ በመሆኑ ይህንን ለመቆጣጠር እና ስርዓት ለማስያዝ የትራንስፖርት ባለሥልጣን በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ይህን ጥረት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እግረኞች በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ የትራፊክ ደንቦችን አክብረው የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ በሕግ መደንገግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 395/2009 ተሸሽሎ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
በተሸሻለው የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ መሠረት የትራፊክ ተቆጣጣሪ ወይም በሕግ ሥልጣን የተሰጠው ሌላ ሰው የዚህን ደንብ ድንጋጌዎችን የተላለፈ እግረኛ ወይም ሌላ ማናቸውም ሰው ላጠፈው ጥፋት የሚገባውን ቅጣት እንዲፈጽም የቅጣት ወረቀት ይሰጠዋል በሚለው መሠረት ዝርዝር አፈጻጸሙን ለተገልጋዩና ለፈጻሚው በመመሪያ ግልጽ ማድረግ በማስፈለጉ በሚንስትሮች ደንብ ቁጥር 395/2009 አንቀጽ16 ንዑስ ቁጥር 3 መሠረት የእግረኞችን የመንገድ አጠቃቀም በሚመለከት ይህ የአፈጻጸም መመሪያ ወጥቷል፡፡