የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ከኀዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲሆን በአዋጅ ቁጥር 916/2008 ተደንግጓል፡፡
ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር ቢሆንም በአዋጅ ቁጥር 25/1984 እና በደንብ ቁጥር50/1991 መሠረት የሕግ የሰውነት መብት ያለውና ራሱን የቻለ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ በአዋጁና በደንቡ ድርጅቱን የማስተዳደር ሥልጣን ተሰጥቷል፡፡ ከዚህም ሥልጣንና ተግባር መካከል የድርጅቱን ንብረት የማስተዳደር ኃላፊነት ነው፡፡
በዚሁ መሠረት የልማት ድርጅቶችን ሥልጣንና ተግባር በሚወስነው አዋጅ ቁጥር25/1984 አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ 6 መሠረት በድርጅቱ ህልውና ላይ ወሳኝነት የሌላቸውን ቋሚ ንብረቶች ሽያጭ በድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ፀድቆ የሚከናወን መሆኑን ሥልጣን የሰጠ በመሆኑ ድርጅቱ አሁን ያለውን በድርጅቱ ህልውና ላይ ወሳኝነት የሌላቸው ከፍተኛ መጠን ያላቸው እና ቋሚ ያልሆኑ ንብረቶች በድርጅቱ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነታቸውን በመገምገም በሽያጭና በሌሎች የማስወገጃ ዘዴዎች ማስወገድ አስፈላጊ በመሆኑ እንዲሁም ከዚህ በፊት እየተሠራበት የነበረውን አሠራር የበለጠ ግልፅ ዘመናዊ ቀልጣፋና ውጤታማ የሚያደርግ የንብረት አወጋገድ ስርዓት ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ ድርጅቱ ይህንን የንብረት አወጋገድ መመሪያ አውጥቷል፡፡