ከ15 ዓመታት ወዲህ መንግሥት የግል ባለኃብቱ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርግ በማሰብ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት በማፋጠን፣ የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በማሰብ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውም ትኩረት እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡
በዚሁ መሠረት የጠቅላላ የአቪዬሽን አገልግሎት የኢንዱስትሪው አካል አንዱ በመሆኑ፣ ዘርፉ እንዲስፋፋ በማድረግ፣ ጤናማ የሆነ ተወዳዳሪነትን በማስፈን ተጠቃሚው የተለያዩ አማራጮች እንዲኖረው እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው በማሰብ በኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 769/2004 ከ50 መቀመጫዎች ያልበለጡ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች በንግድ ሥራው እንዲሳተፉ በአዋጅ ተፈቀደ፡፡
የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ከ30 በላይ የግል ባለኃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው መንቀሳቀስ ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ካንፓኒውን ለማቋቋም እንዲሁም የንግድ ሥራው ለማስኬድ ከፍተኛ የካፒታል ወጪ (the high capital costs of establishing and running airlines) ስለሚጠይቅ፣ ለዘረፍ በልዩ ሁኔታ የሰለጠነ የሰው ኃይል ገብያ ላይ በስፋት ለማግኝት አዳጋች በመሆኑ እና በሌሎች በራሳቸው ምክንያት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ ተመናምነው በአሁኑ ወቅት እስከ 8 የሚደርሱ ኦፕሬተሮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም አቢሰኒያ የበረራ አገልግሎት ትራንስ ኔሽን ኤይርዌይስ፣ አኳሪየስ አቪዬሽን፣ ናሽናል ኤይርዌይስ፣ ዘመን የበረራ አገልግሎት፣ኢስት አፍሪካ አቪዬሽን፣ ዋሊያ ኤርዌይስ፣ አሚባራ የእርሻ ልማት ድርጅት ኦፕሬተሮች በአብዛኛው የቻርተር ፣ የአንቡላንስ ፣ የጭነት እና የርጭት አገልግሎት መደበኛ ያልሆኑ በረራዎች በሀገር ውስጥ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ለማሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመውሰድ ወደ ቢዝነስ ስራ ለመግባት እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ አዳዲስ ባለሃብቶችም ይገኛሉ፡፡
ተቆጣጣሪ ባለስልጣኑ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች አንዱና ዋናው ውስጥ የአቪዬሽን እንዱስትሪው በአገሪቱ እንዲስፋፋ ማድረግ ሲሆን በተለይ የግል ዘርፉ በአየር አገልግሎትና ለጠቅላላ የአቪዬሽን አገልግሎት ለመሳተፍ የስራ ፈቃድ ከመስጠት ባሻገር ተያያዥ መመሪያዎችን በማዘጋጀት እና ቁጥጥር በማድረግ የግል የአቪዬሽን ዘርፉ የተፈለገው እድገት እንዲያስመዘግቡ መርዳት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ በተለይ በግል ኦፕሬተሮች ተዘውትረው የሚነሱ ለሥራዎቻቸው እንቅፋት የሆኑ ችግሮች በመለየት ለዘርፉ እድገት አፋጣኝ የሆኑ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡
የግል ኦፕሬተሮች መስፈርቱ በሚጠይቀው አሟልተው የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው አስፈላጊው ማበረታቻ (Incentives) ተደርጎላቸው ፣ ንግድ ፈቃድ እና የአየር ኦፕሬተር ሰርተፍኬት ወስደው ወደ ንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ከገቡ በኋላ በሀገር ውስጥ፣ በአጎራባች እና በሌሎች ሀገራት የሚሰጧቸው የበረራ አገልግሎት ግልጽነት የተላበሰ እንዲሆን፤ ከገልግሎቱ ለዜጎች በተፈለገው መጠን የስራ እድል በመፍጠር እንዲቻል እንዲሁም ከተገኝው ገቢ እና ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ለመንግሥት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የፋይናንስ መመሪያው ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ይህ የፋይናንስ መመሪያ ትኩረት የሚያደርግባቸው በዋናነት የግል ኦፕሬተሮች ወቅታዊ የአየር ትራንስፖርት እስታትስቲክስ የተሳፋሪ፣ የጭነት አገልግሎት፣ የሥልጠና እና ተያያዥ መረጃዎች እንዲያቀርቡ፣ የፋይናንስ አቋም መረጃዎች ማለትም ወቅታዊ የገቢና የወጭ መረጃዎች ፣ በውጪ የሚደረጉ ኦፕሬሽኖች (በረራዎች) የፋይናንስ ዝውውር መረጃ እና የባንክ ማረጋገጫ የሂሳብ መግለጫዎች እንዲሁመ ኦፕሬተሮች የአውሮፕላን ኪራይና ግዥ ሲፈጽሙ የገንዘብ ዝውውር ሁኔታ ሰነድ የያዙ መረጃዎች የተመለከቱ ጉዳዮች ለተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በየወቅቱ ማሳወቅ እንዳለባቸው ትኩረትን በማድረግ የተዘጋጀ የፋይናንስ አፈጻጸም መመሪያ ነው፡፡
በመጨረሻም መመሪያው በአባሪነት የግል ኦፕሬተሮች በኢትዮጽያ ያለበት ሁኔታ የግል ኦፕሬተሮች አገራዊ እና አለማቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ፣ የግል የአየር ኦፕሬተሮች ኢኮኖሚያዊ አስተዋጾኦ፣ የአየር ትራንስፖርት የኢኮኖሚ ሬጉሌሽን በፋይናንስ እይታ፣ የኦፕሬተሮች የኢኮኖሚ ቁጥጥር አግባቦች ተሞክሮ በመጨረሻም የሚፈለጉት መረጃዎች ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ቅጾች አካቶ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡