የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ለከተማው ነዋሪ የሚሰጠውን የአጠቃላይትምህርት አገልግሎት ግልጽ፣ ፈጣንና ውጤታማ እንዲሆንና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በርካታ የለውጥ ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከነዚህ ለውጦች መካከል ከቢሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የአጠቃላይ ትምህርት አደረጃጀቶችን እንደገና በማደራጀት ወደ ስራ መግባቱ ዋና ማሳያ ነው፡፡ በዚህም በቢሮ በ 9 ዓላማ ፈፃሚ ዳይሬክቶሬቶች፣ በክ/ከተማ በ 6 ቡድኖችና የሱፐርቪዥን ክላስተር ቡድኖች፣ በወረዳ በ 2 ቡድኖችና የሱፐርቪዥን ክላስተር ቡድኖች ተደራጅቶና የሰራተኞች ድልድል በመመሪያው መሠረት ተካሂዶ በአዲስ አደረጃጀትና በተለወጠ ሠራተኛ ስራ በመጀመሩ፤
ይህ የለውጥ አሠራር ዳር እንዲደርስና ውጤታማ እንዲሆን የትምህርት ሴክተሩ ዋና አካል የሆነው ትምህርት ቤት በመዋቅራዊ አደረጃጀቱ እንደገና ሊቃኝና ዋና ር/መምህራንና ም/ር/መምህራን በአዲስ መንገድ ሊደለደል ስለሚገባ አዲስ የትምህርት ቤቶች መዋቅርአደረጃጀት በመዘጋጀቱ፤
በዚህ መዋቅራዊ አደረጃጀት ጥናት ለተዘጋጁት ሁለቱ የስራ መደቦች ከመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ጋር የሚጣጣም የአፈፃፀም መርህና ቅደም ተከተልን መሠረት ያደረገ በጥናቱ ለሥራ መደቦቹ በተሰጠው ደረጃ ለማወዳደር እና ለመደልደል የሚያስችል አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የአስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማቋቋም ጸድቆ በወጣው አዋጅ ቁጥር74/2014 አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ (2) (ሠ) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን በትምህርት ቤት መዋቅር ክለሳ ጥናት ለተዘጋጁ የሥራ መደቦች የዋና ር/መምህራንና ም/ር/መምህራን የድልድል አፈፃፀም መመሪያ አውጥቷል፡፡