በኢትዮጵያ ከሚገኙት ከተሞች መካከል ከ85% በላይ የሚሆኑት በአነስተኛ ከተማነት ማለትም የሕዝብ ቁጥራቸው ከ20,000 በታች የሆነ ነዋሪ የሚገኙባቸው ከተሞች ናቸው፡፡ በአገራችን ከ8ዐ% በላይ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረው በገጠር አካባቢ ሲሆን የገጠር አካባቢ ነዋሪውም በአብዛኛው አገልግሎቶችን የሚጋራው ከነዚሁ ከተሞች ነው፡፡ የገጠሩን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻልና ልማትን ለማፋጠን እንደዚሁም የገጠርና የከተማን ትስስር ለማጠናከር የእነዚሁ አነስተኛ ከተሞች ልማት ወሳኝ ነው፡፡ በነዚሁ ከተሞች ላይም አስፈላጊውን ልማት ለማምጣት መሠረታዊ ጉዳይ የሚሆነው ከተሞቹ የሚመሩበትን የከተማ ፕላን በቅድሚያ ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ ባለፉት አመታት በአነስተኛ ከተሞች ዙሪያ የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም ቁጥራቸው ከ483 ያላነሱ ከተሞች የፕላን ተጠቃሚ ሆነዋል። ሆኖም ፕላን ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ከተሞችም ቢሆኑ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ከተሞች የፕላን ክለሣ የሚፈልጉ መሆናቸው ይታመናል፡፡
በተመሳሳይም ቁጥራቸው ከ15,000 የማያንሱ የገጠር የቀበሌ ማዕከላት መኖራቸውም ወደፊት እነዚህ ማዕከላት ጭምር ቁጥራቸው እያደገ ሲሄድ የከተማነት መስፈርትን በማሟላት ወደ ከተማ መቀየራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በተመሳሳይም ከ2ዐዐዐ ሕዝብ በላይ ያላቸው ከተሞችም የእድገት ሁኔታ ፈጣን እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐንም ብሔር ብሄረሰቦች አካባቢያቸውን እያስተዳደሩ በመሆናቸው ለአካባቢው ልማት ቀናና ምቹ ሁኔታ በመፈጠር ላይ በመሆኑ ለከተሞቻቸው ልማት የፕላን ጉዳይን እንደ ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጡት ይገኛል፡፡ የከተማ መሠረታዊ ካርታ ከማዘጋጀት ጋር በተያያዘም የሳተላይት ምስልን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ለበርካታ ከተሞች መሠረታዊ ካርታ ማዘጋጀት የሚቻልበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በመሆኑም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እነዚሁ እያደጉ የሚገኙ ከተሞችን በፕላን እንዲመሩ ከማድረግ አኳያ እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ እስከአሁን ባለው ሁኔታ የከተማ ፕላን ዝግጅት በአብዛኛው በመንግሥታዊ ተቋማት አቅም ላይ ባተኮረ መልኩ የሚዘጋጅና የግል አማካሪዎች ተሳትፎ ውስንነት ይታያል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ እምቅ አቅም ያላቸው ባለሙያዎችን በማሰባሰብ፣ በማደራጀትና ሥልጠና በመስጠት ወደ መስኩ እንዲገቡና የግሉ ዘርፍ የእንቅስቃሴ ሚና ከፍ እንዲል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በአነስተኛ ከተሞች የመሠረታዊ ፕላን ዝግጅት ዙሪያ የሚሳተፉ የአማካሪ አሀዶችን በተከታታይና በስፋት ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ የሚ/ር መ/ቤቱ የማብቃት ሥራዎችን በመሥራት ወደ መስኩ ለማስገባት የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡
በመሆኑም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 691/2ዐዐ3 አንቀጽ 25/1/ቸ/ ሥር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል።