የመመሪያ መለያ: 323/2013
ቀን: ታህሳስ 14፥ 2013 ዓ.ም.
Language: Amharic

የገቢ ከፍተኛ ጭነት አመጣጥን በብሔራዊ ደረጃ ለማቀናጀትና ለመቆጣጠር የወጣ መመሪያ ቁጥር 323/2013

አገራችን ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በማስመዝገብ ላይ ባለችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እና ልማቱ በፈጠረዉ ከፍተኛ መነቃቃት ወደ አገር ዉስጥ ምናስገባዉ የገቢ ዕቃ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነትም ሆነ በመጠን እየጨመረ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ይህን ከፍተኛ እድገት ተከትሎ በሁሉም ሊባል የሚችል በመፍትሄ ዙሪያ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከንግድ እንቅስቃሴ ማደግ ጋር የተመጣጠነ ባለመሆኑ በሎጅስቲክስ አቅርቦትና አጠቃላይ በዕቃ አነሳስና የማጓጓዝ ሂደት ላይ ጉልህ ችግር ተከስቷል፡፡ ይህ ችግር የሎጅስቲክስ ጊዜ ማራዘምና የሎጅስቲክስ ወጪ ማናር ከሚያስከትለው ጉዳቶች በላይ በሀገር ገጽታ (mage) ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በመሆኑም ይህ ችግር መቀጠል የለበትም፡፡ ሁሉም አካል ችግሩ እንዲቀጥል መፍቀድ አይኖርበትም፡፡

የሀገሪቱ ዋና ዋና ገቢ ዕቃዎች ነዳጅ ፣ ደረቅ ብትን ጭነት እና ጀነራል ካርጎ ሲሆን የሀገሪቱ የብትን ጭነት ደግሞ በዋናነት ማዳበሪያ፣ የእርዳታና የግዢ እህል፣ ሲሚንቶ፣ ስኳር እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የድንጋይ ከሰል ሲሆን ከአገራችን ገቢ ዕቃዎች ውስጥ በክብደት በአማካይ 5ዐ% ያህል ነው፡፡ የከፍተኛ መጠን ጭነት (Bulk Shipment) አስመጪዎች በዋነኛነት መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡

ይህ ጭነት በአንድ ጊዜ (lot) ከፍተኛ ክብደት የመጫን አቅም ባላቸው የጭነት አጓጓዥ መርከቦች (Bulk Carriers) የሚጓጓዝ ሲሆን በአብዛኛው በአንድ ጊዜ (lot) ከ25,000-30,000 ቶን አንዳንድ ጊዜም በአንድ ጊዜ 50,000 ቶንና ከዛ በላይም ይጓጓዛል፡፡ ጭነቱን የሚያጓጓዙት መርከቦች በወደብ ማሸጊያ (Berth) ተጠግተው ለመስተናገድ ከፍተኛ ጥልቀት (Draft) የሚጠይቁ ትላልቅ መርከቦች ናቸው፡፡ የጭነቱ የኦኘሬሽን ባህሪው መሬት ሳይራገፍ ከመርከብ በቀጥታ በተሽከርካሪዎች ላይ በመጫን (Direct Delivery Operation) የሚጓጓዝ ነው፡፡ በመሆኑ ጭነቱ ከመርከብ ተራግፎ በቀጥታ በተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጫን የሚደረግበት ሂደት እንዳይስተጓጎል ማድረግ ከተቻለ በወደብ ሊኖር የሚገባውን ተገቢ የመርከብ ቆይታ ጊዜ በመጠበቅ በወደብ የመርከብ ማሸጊያ መጣበብንና የወደብ መጨናነቅን ለመከላከል ይቻላል፡፡

ኦፕሬሽኑ በተፈለገው ተገቢ ጊዜ እንዳይከናወን ሂደቱን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ሁኔታዎች የሚከሰቱበት አጋጣሚዎች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህም መካከል በዋነኛነት የመርከቦች አመጣጥ ቅደም ተከተል፣ ከወደብ የማስተናገድ አቅም አኳያ ተገናዝቦ ዕቅድ ላይ ሳይመሠረት በተመሣሣይ ወይም በተቀራራቢ ጊዜ ውስጥ ወደ ወደብ ተደራርቦ መምጣት፣ በአገር ውስጥ የማከማቻ ሥፍራ / መጋዘን/ ዝግጅት ችግር ፣ የተሽከርካሪዎች አቅርቦት እጥረት፣ በወደብና በመርከብ መሣሪያና አሠራር ምክንያት የሚፈጠር የወደብ ዕቃን የማንሳት ውሱንነት የመሳሰሉ ችግሮች ሲያጋጥሙ የመርከብ የወደብ ላይ ቆይታ ጊዜ የሚራዘምበት እንዲሁም፤ ጭነቱ በወደብ ውስጥ መሬት ላይ እንዲራገፍ እና ወደ ወደብ መጋዘን ተጓጉዞ እንዲከማች የሚያስገድድ ሁኔታ የሚፈጠር ሲሆን ይህም አላስፈላጊ ወጪ እና ተያያዥ ችግሮችን ያስከትላል፡፡

የችግሮቹ ተፅዕኖ ከወጪ አንጻር ቢታይ የመርከብ የወደብ ላይ ቆይታ ጊዜ በመራዘሙ ምክንያት የሚፈጠር ክፍያ (Demurrage)፤ በወደብ ለመስተናገድ ተጨማሪ ኦፕሬሽን ውስጥ በመግባት ምክንያት (charges due to double operation) የሚፈጸም ክፍያ፤ ማለትም ጭነቱ በወደብ ውስጥ መሬት ላይ ከተራገፈ በኋላ ለሚሰጥ አገልግሎት /shore handling/ ተጨማሪ ወጪ ያስከትላል፤ ወደ ወደብ መጋዘን ከተጓጓዘ ደግሞ ከዚህ በላይ ለከፍተኛ የማከማቻ ተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ ይሆናል፡፡

ችግሮቹ ከዚህም ባለፈ ለመርከብ ማሸጊያ (Berth) መጣበብና የወደብ መጨናነቅ፤ ኢኮኖሚያዊ የተሸከርካሪ አጠቃቀምን በማወክ የሚፈጠር የተሸከርካሪ እጥረት፣ ዕቃው በተፈለገው ወቅት ለተፈለገው ዓላማ በወቅቱ ያለመድረስ እና በግብይት ሥርዓት ላይ የሚፈጠር የዋጋ መናር ወዘተ የሚያስከትሉ በመሆኑ በአስመጪዎች፣ በወደብ፣ በላኪዎችና በኦኘሬተሮች መካከል አለመግባባት እና ከፍተኛ ቅሬታና ተያያዥ ችግሮችን አስከትሏል፡፡

በመሆኑም የሀገራችን የገቢ ዕቃዎች ንግድ ልማት ለመደገፍ መከናወን ካለባቸው ቁልፍ ተግባራት ውስጥ አንዱ የትራንዚት ወጪና ጊዜን ለመቀነስ የሚያስችል የትራንዚት ሥርዓት እና የገቢ ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በአጭር ጊዜ ለማጓጓዝ የሚያስችል የአሠራር መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የአገሪቱ የገቢ ንግድ በሚፈለገው ደረጃ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ የተረጋገጠ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀልጣፋ የወደብና የትራንዚት አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል እንዲሁም የገቢ ብትን ጭነት ብቻ ሳይሆን በአንድ ጊዜ (lot) ከፍተኛ መጠን ያላቸው የገቢ ጭነት ክምችት በባህር ወደብ እንዳይኖር እና ተቀናጅቶ እንዲገባ የሚያደርግ የአሠራር መመሪያ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ የግድ ይላል፡፡

በዚህ መሠረት ከፍተኛ መጠን ጭነት (Bulk Shipment) የትራንዚት ሥርዓት የሚመራበትን ስታንዳርድ አሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እና የሚመለከታቸው አካላት እስካሁን ተግባራዊ እያደረጉ የቆዩት ተግባርና ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የገቢ ንግድ ልማት መስኩ የታለመለትን ዓላማ ያሳካ ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነቶችና ግዴታዎች ለመወሰን በማሪታይም ዘርፍ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 549/1999 አንቀጽ 18 (ለ) ለሚኒስቴሩ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህ መመሪያ ወጥቷል፡፡

PDF Document

Tap the button below to view or download this PDF.

View PDF

ተጨማሪ መረጃዎች

መመሪያውን ያውርዱ

የኢፌዲሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር

FDRE Ministry of Transport

Similar Directives

ሰኔ 18÷2018
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር
Ministry of Trade and Regional Integration
ሰኔ 18÷2018
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር
Ministry of Trade and Regional Integration