ባለሥልጣን መ/ቤቱ፣ በዋና መ/ቤት፣ በቅርንጫፍ እንዲሁም በፕሮጀክት ፅ/ቤት የሚገኙ የሰው ኃይል አስተዳደር ደጋፊ የሥራ ሂደት እና ቡድኖች በመ/ቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ክፍት የስራ መደቦችን በደረጃ እድገት፣ በዝውውር፣ በቋሚ ቅጥር እንዱሁም በኮንትራት ቅጥር በተዘጋጀው የሰው ኃይል አስተዳደር የአፈፃፀም መመሪያ መሠረት እያሟላ ቆይቷል፤
በሰው ኃይል አፈፃፀም መመሪያው በደረጃ እድገት እንዲሁም በዝውውር የሚደረጉ የሰው ኃይል ማሟላት ሂደቶች በሥራ ልምድ፣ በትምህርት ዝግጀት፣ በሥራ አፈጻጸም እና በማህደር ጥራት ላይ ብቻ በመመስረት የሚከናወኑ በመሆኑ በመስፈርትነት ሥራ መደቡ የሚጠይቀውን ክህሎት ለማረጋገጥ የሚሰጥ የመመዘኛ ፈተና ባለመኖሩ በመ/ቤቱ ስራ አፈፃፀም ላይ ክፍተት እየተፈጠረ የሚገኝ በመሆኑ፣ ቋሚ እና ኮንትራት ቅጥርን በተመለከተ በአፈፃፀም መመሪያው የፈተናና የውጤት አሰጣጥ ሂደቱ ተፈላጊውን ብቁ የሰው ኃይል ለማግኘት እያስቻለ ባለመሆኑ፤
ይህንን ክፍተት ለመቅረፍ መ/ቤቱ ክፍት የሥራ መደቦችን ለማሟላት የሥራ መደቦች የሚያስፈልገውን እውቀት እና ክህሎት ለማረጋገጥ የሚሰጥ የመመዘኛ ፈተና በተጨማሪ መስፈርትነት ማካተት እና ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረውን የፈተና ሂደት መቀየር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 35/2004 አንቀጽ 53 ንዑስ አንቀጽ 2 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡