ሀገራችን ከማዕድን ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው መንገዶች አንዱ የከበሩና በከፊል የከበሩ ጌጣጌጥ ማዕድናት ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ነው፡፡ ግብይቱም የሚሳለጠው በላኪዎችና በዕደ ጥበብ /የላፒደሪና የስሚዘሪ/ ባለፈቃዶች በኩል በሚፈጠረው የገበያ ትስስር ሲሆን ከዚህ ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ ማዕድናትን በመምረጥ ግብይት መፈፀም እንዲሁም በዕደጥበብ እና ከልዩ አነስተኛ ማዕድን ማምረት ስራ ፈቀድ ጋር የተያያዙ የቴክኒክ ስራዎች ላይ በተቀጣሪነት የውጭ ዜጎችን ማሰተፍ የሚያስችል አሠራር በዚህ መመሪያ ውስጥ ማካተት በማስፈለጉ ፤
በሌላ መልኩ በዚህ ግብይት ላይ የሚሳተፉ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ማዕድን ምርት ቦታ ሳይሄዱ ማዕድናትን በጥሬው ወይም በጌጥ መልክ ከተዘጋጀ በኋላ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ፈቀድ ካላቸው ባለፈቃዶች ጋር በመገናኘት የሚቀርበውን ማዕድን መለየትና መግዛት እንዲችሉና ከዚህ በፊት ወደ ማዕድን ምርት ቦታ የሚሄዱበትን አግባብ ማስቀረትና የግብይት ሥርዓቱ ሕግን መሠረት ባደረገ አግባብ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፤
ማዕድናትን በጥሬው ወይም በጌጥ መልክ ከተዘጋጀ በኋላ ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ ፈቀድ ያላቸው ባለፈቃዶችም በውጭ ሀገር ከሚገኙት የማዕድን ተረካቢዎቻቸው ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲችሉ፣ ግብይቱን የሚፈጽሙ የውጭ ሀገር ዜጎችም ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡና ከባለፈቃዶች ጋር ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ መሥራት እንዲችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት፣ እንዲሁም ሕጋዊና ፍትሃዊ የግብይት ሥርዓት እንዲሰፍን ለማስቻልና የከበሩ ማዕድናት ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ስራን ለማስተዳደር እንዲቻል በከበሩ ማዕድናት ግብይት አዋጅ ቁጥር 651/20017 አንቀጽ 31 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ይህ መመሪያ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡