የባለሞተር ተሸከርካሪዎች የንግድ ሥርዓት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወደም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብንና ሽብርተኝነን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለሚፈጽሙ ወንጀለኞች መደበቂያ ዘርፍ መሆኑን ጥናቶች የሚያረጋግጡ በመሆኑ፤
የባለሞተር ተሸከርካሪ ነጋዴዎችን ስራ ተጠያቂነትና ግልጸኝነትን ለማረጋገጥ አስቻይ ከባቢ በመፍጠር በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወደም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብንና ሽብርተኝነን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብንና ሽብርተኝነን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አኳያ የባለሞተር ተሸከርካሪዎች የንግድ ዘርፍን የሚመራ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊነቱ የታመነበት በመሆኑ፤
የባለሞተር ተሸከርካሪዎች የንግድ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በአዋጁና በመመሪያው ውስጥ የተደነገጉ ግዴታዎቻቸውን እንዲወጡ የውስጥ የአሠራር ስርዓቶች አና ማኑዋሎች እንዲኖራቸውና ስጋቶችን በራሳቸው አቅም እንዲለዩ ለማድረግ አቅማቸውን ማጎልበት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የባለሞተር ተሸከርካሪ ነጋዴዎች ደንበኞቻቸውን እንዲለዩ ለማስቻልና በዚህም የወንጀሎቹ መፈጸሚያ መሳሪያ እንዳይሆኑ መጠበቅ/መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ፤
በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 2(10) (ሠ) እና በአንቀጽ 54(2) መሠረት የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የሚከተለውን መመሪያ አውጥቷል፡፡