ባለስልጣኑ የደንበኞች የውሃ አገልግሎት አሰጣጥ ወጥነት ያለው የአሠራር ስርዓት በመዘርጋት ደንበኞች አገልግሎትን ለማግኘት ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በግልጽ ለማስቀመጥ በማስፈለጉ፡፡
የባለስልጣኑ ሰራተኞች ባለስልጣኑ ለደንበኞች የሚሰጠው አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀና በጊዜ የተገደበ መሆኑን በመገንዘብ ስራዎችን በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሠረት በመፈፀም የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ለማስቻልና ይህ ባይሆን ደንበኞች በአግባቡ ቅሬታ ለማቅረብ የሚያስችላቸውን አሠራር መዘርጋት በማስፈለጉ፡፡
የቆጣሪ ንባብ ጥራት በማሳደግ የገቢ አሰባሰቡን ለማሳደግና በተለያየ ምክንያት ያለባቸውን ሂሳብ በአንድ ግዜ አጠቃለው ለመክፈል አቅም ላጡ ደንበኞች የክፍያ ጊዜ በመስጠት ሂሳባቸውን ለማስከፈል እንዲሁም የደንበኞችን መረጃ በዘመናዊ መልክ ማደራጀትና መረጃዎችንም በተፈለገው ጊዜ በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል አሠራር ስርዓት መዘርጋት አስፈሊጊ መሆኑ ስለታመነ፤
ባለስልጣኑ ለደንበኞች የሚሰጣቸው የአዲስ ውሃ ቅጥያ፣ ማዘዋዋሪያ፣ ማሻሻያ፣ ቦኖ፣ የቦቴ ውሃ፣ የሮቶ ውሃ፣ የተንቀሳቃሽ ቦኖ ውሃ፣ የቆጣሪ ንባብ፣ የገንዘብ አሰባሰብ ፣ የጥገና አገልግሎቶች ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ፈጣን በማድረግ አገልግሎቱም ደንበኞችን ፍላጎት የሚያረካ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት ወጥ የሆነ አሠራር ማስፈን ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 35/2004 አንቀጽ 53 ንዑስ አንቀጽ 2 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡