ባለስልጣኑ የከተማውን ነዋሪ የውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካት እና አሰራሩን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ እና ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ ለማድረግ ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀመጥ እና ስራዎች የሚከናወኑበትን ስታንዳርድ በማውጣት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ በመሆኑ፤
ይህም የባለስልጣኑ ዓላማ ግቡን ይመታ ዘንድ የደንበኞችን መብት፣ ተግባር እና ኃላፊነት በግልፅ ለይቶ ማስቀመጥ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፤
የባለስልጣኑ ከደንበኞቹ ጋር ያለው አስተዳደራዊ እና ኦፕሬሽናል ግንኙነት ግልፅ፣ ተገማች እና ወጥነት ያለው እንዲሆን በማስፈለጉ፤
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 35/2004 አንቀጽ 53 ንዑስ አንቀጽ 2 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡